ትውልደ ኤርትራዊው የኒው ዚላንድ የሕዝብ እንደራሴ አባል ሆኖ ተመረጠ

ኢብራሂም ኦመር

የፎቶው ባለመብት, Labour Party

የምስሉ መግለጫ, ኢብራሂም ኦመር
ታትሟል

በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ኒው ዚላንዳውያን ትውልደ ኤርትራዊውን የሕዝብ እንደራሴ አባል አድርገው መረጡ።

ይህም ትውልደ ኤርትራዊው ኢብራሂም ኦመር በኒው ዚላንድ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የፓርላማ አባል አድርጎታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ሌበር ፓርቲ በ50 ዓመት ታሪኩ ከፍተኛውን ድል ማግኘቱን ተከትሎ ነው ኢብራሂም ኦመር የኒው ዚላንድ የፓርላማ አባል መሆን የቻለው።

የአሁኑ የፓርላማ አባል የቀድሞው ኤርትራዊ ስደተኛ ኢብራሂም ኦመር በምረጡኝ ቅስቀሳው ''እሱ በነበረበት ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎችን የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው እንደሚሰራ'' ገልጾ ነበር።

ኢብራሂም ኦመር ከኤርትራ የወጣው በአውሮፓውያኑ 2003 ሲሆን በወቅቱ በጎረቤት አገር ሱዳን በስደተኞች ማቆያ ካምፕ ውስጥ ቆይቷል። በመቀጠልም ወደ ኒው ዚላንድ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ በቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በጽዳት ሰራተኝነት አገልግሏል።

በጽዳት ሰራተኝነት ባገለገለበት ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን የተከታተለው ኢብራሂም ኦማር እዛው እያለ ነበር ወደ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የገባው።

ለፓርላማ አባልነት ከተመረጠ በኋላ ኢብራሂም ኦማር ''የእኔ ድል ለሁሉም ዝቅተኛ ተከፋዮችና ለቀድሞ ስደተኞች ድል ነው'' ብሏል።