ኮሮናቫይረስ፡ ጣሊያን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ዳግም ጥብቅ መመሪያዎችን አስተላለፈች

ጣሊያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በጣልያን የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በድጋሚ ማንሰራራቱን ተከትሎ አገሪቱ በርካታ ጠበቅ ያሉ የእንቅስቃሴ ገደብና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምራለች።

አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርገው ብቅ ያሉት የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉሴፔ ኮንቴ ጥብቅ የጥንቃቄ እርምጃውን መውሰድ ያስፈለገው አዲስ ሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብን ለማስቀረት በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአዲሱ ውሳኔ መሠረት የከተሞች ከንቲባዎች ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎችን ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ እንዲዘጉ የማድረግ ስልጣን ያላቸው ሲሆን በተጨማሪም ምግብና መጠጥ ቤቶች መቼ ይከፈቱና ምን ያክል ሰው ያስተናግዱ የሚለውንም የመወሰን ስልጣን አላቸው።

ጣልያን ይህንን እርምጃ የወሰደችው በቅርብ ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ሲሆን ለተከታታይ ሁለት ቀናትም በቀን ውስጥ ከፍተኛውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች።

ተጨማሪ 11ሺ 705 ሰዎች ዕሁድ ዕለት በቫይረሱ መያዛቸውም ተገልጿል። ቅዳሜ ደግሞ በአንድ ቀን ብቻ 10ሺ 925 ሰዎች በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ጣልያን በመጀመሪያዎቹ የቫይረሱ ስርጭት ወራት በእጅጉ ተጎድታ የነበረ ሲሆን እስካሁን በአገሪቱ በአጠቃላይ 414ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች። በተጨማሪም በዚሁ ቫይረስ ምክንያት 36 ሺ 500 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚንስትር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚንስትር

ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ እንዳሉት ከሆነ አገሪቱ ምንም አይነት ጊዜ ማባከን አትፈልግም። ''ለዚህም ሲባል ፈጣን የሆነ ምላሽ መስጠት በማስፈለጉና ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብን ለማስቀረት ሲባል ከዚህ ውሳኔ ደርሰናል'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አክለውም ''በጣም ውጤታማ የሚባሉት የጥንቃቄ እርምጃዎች በጣም ቀላሎቹ ናቸው፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እና የግል ንጽህናን በአግባቡ መከታተል ናቸው'' ብለዋል።

በአዲሱ ሕግ መሰረትም ስብሰባዎችና የሕዝብ በአላትን ሰብሰብ ብሎ ማክበር የተከለከለ ሲሆን ጀማሪ ስፖርተኞች የሚካካፈሉባቸው የስፖርት ውድድሮችም ለጊዜው እንዲቋረጡ ተብሏል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያዎችና የዋና ገንዳዎች በተመለከተም በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት አዲስ መመሪያ እንደሚወጣ ተገልጿል።