ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለሀብቱ በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ በተባለ የታክስ ስወራ ተከሰሱ
አሜሪካዊው ባለሀብት በአገሪቱ ታሪክ ትልቁ በተባለ የታክስ ስወራ ክስ ተመሰረተባቸው።
ሮበርት ብሮክማን፤ ሬይኖልድስ ኤንድ ሬይኖልድ የተሰኘ የኮምፒዩተር ሶፍትዌር አምራች ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት፤ ያገኙትን 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከአሜሪካ መንግሥት ደብቀዋል ተብሏል።
ሮበርት ብሮክማን ከአሜሪካ መንግሥት 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ የሰወሩት ገንዘቡን በሌሎች አገራት ከሚገኙ ኩባንያዎቻቸው የተገኘ በማስመሰል ነው ተብሏል።
ብሮክማን በቴሌኮንፍረስን አማካኝነት በሂውስተን ቴክሳስ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ ለቀረቡባቸውን ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም ብለው ተከራክረዋል።
ባለሀብቱ በአጠቃላይ 39 ክሶች የተመሰረቱባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የታክስ ስወራ እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመሰል የሚሉት ይገኙበታል።
ብሮክማን ይህን የታክስ ስወራ ወንጀል ስለመፈጸማቸውን ለአሜሪካ መንግሥት ጥቆማ ያደሩት ደግሞ ሮበርት ስሚዝ የሚባሉ ሌላ ሚሊየነር የንግድ ሰው ናቸው።
ሮበርት ስሚዝ በተመሳሳይ የገቢ ምንጮቻቸውን በመደበቅ ታክስ ሲያጭበረብሩ እንደነበረ ያመኑ ሲሆን፤ መንግሥት ክስ እንዳይመሰርትባቸው ብሮክማን ላይ ጥቆማ ሰጥተዋል ተብሏል።
ሮበርት ስሚዝ ጥቆማውን ለአሜሪካ መንግሥት የሰጡት ለፈጸሙት የታክስ ማጭበርበር ክስ እንደማይሰመረትባቸው ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ነው ተብሏል።
ይሁን እንጂ ሮበርት ስሚዝ 139 ሚሊዮን ዶላር በቅጣት መልክ ለአሜሪካ መንግሥት ክፍያ ለመፈጸም ተስማምተዋል።