አማራ ክልል፡ ባለፉት ሦስት ወራት ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል

ታትሟል

አቶ ሃብታሙ ሃይሌ የምዕራብ ጎንደር ዞን የገንደ ውሃ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እንደ አቶ ሃብታሙ ከሆነ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአካባቢው የወባ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

"ቁጥሩ ጨምሯል። . . . ሁሌም በዚህ ወቅት የወባ በሽተኞች ቁጥር ይጨምራል። አሁን ግን ከበፊቱ እየጨመረ እያየን ነው" ሲሉ ይገልጻሉ።

"ምንም የተለየ ምክንያት የለም። ዘንድሮ ኬሚካልም ሆነ የአጎበር ስርጭት ለህብረተሰቡ ተካሂዷል። የተለየ የሚያደርገው የዝናቡ መጠን ጨምሯል። ከፍተኛ ዝናብ ነበር። ይህ ደግሞ ለወባ መጨመር ምክንያት ነው" ሲሉ ምክንያት የሚሉትን ተናግረዋል።

በአካባቢው በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ቢገልጹም በዚህ ምክንያት ህይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ ጠቁመዋል።

በወባ የሚያያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ደጋግመው የተናገሩት አቶ ሃብታሙ በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በህክምና ተቋማት ህክምና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው ስለ አጎበር አጠቃቀም ትምህርት መሰጠቱትንና በወባ ላይ የሚሠሩ የህክምና ባለሙያዎች በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ እየሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በአካባቢያቸው ከነሐሴ ወር ጀምሮ በወባ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በመተማ ወረዳ ጤና ጥበቃ የወባ ኦፊሰር የሺሃረግ አያናው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ካለፉት አምስት ዓመታት አንጻር በአካባቢው ከፍተኛ የሚባል ለውጥ የለውም ያሉት ወይዘሮ የሺሃረግ ባለፉት ጥቂት ወራት ግን ቁጥሩ ማሻቀቡን ገልጸዋል።

ከሳምንት ሳምንት ቁጥሩ እየጨመረ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎችም ከፍተኛ ቁትር መመዝገቡን ጠቁመዋል።

በአካባቢው ያሉ የቀን ሠራተኞችን ጨምሮ ብዙዎቹ አዲስ በወባ የተጠቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኬሚካል ርጭት በቂ ባይሆንም እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው ዘግይቶም ቢሆን አጎበር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እየተከፋፈለ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ችግሩን ለመቅረፍም ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስ እና በማዳፈን እንዲሁም የተቃጠለ ዘይት በመጠቀም እየተከላከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በክልሉ የወባ ስርጭት ከሳምንት ሳምንት እየጨመረ ይገኛል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ማስተዋል ወርቁ ናቸው።

ከመስከረም እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት የወባ ስርጭት መጨመሩ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸው ሆኖም የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ የክልሉ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ለወባ መራቢያ ምቹ መሆን፣ የማህበረሰቡ ቁጥጥር እና መከላከል ሥራ መቀነስ እና የአልጋ አጎበር አጠቃቀም እና ትኩረት ለኮሮናቫይረስ በመደረጉ ቁጥሩ ከሚጠበቀው በላይ አንዲመዘገብ አድረጓል ብለዋል።

እንደአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ከሆነ በ2012 በጀት ዓመት በክልሉ በወባ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በ2011 ዓመት ከነበረው 66 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የ2012 በጀት ዓመትን የመጀመሪያ ሦስት ወራት ከሐምሌ 1/2012 ጀምሮ ካሉት ሦስት ወራት ጋር በማነጻጸር አራት በመቶ ጭማሪ እንዳለው ወይዘሮ ማስተዋል ገልጸዋል።

በክልሉ ነፍሰጡር እናቶች እና ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ይበልጥ በወባ ተጠቂ መሆናቸውን እና ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ ባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች የክልሉን 88% የወባ ስርጭት ይይዛሉ።

የኬሚካል እና የአጎበር ስርጭት እጥረት መኖሩን ጠቁመው ኬሚካል መረጨት ያለባቸው አካባቢዎች ጭምር እንዳልተረጩ ገልጸዋል።

ክልሉ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ በ53 ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት እንዲካሄድ ጥያቄ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ባለው እጥረት ምክንያት በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ካለመከናወኑም በላይ በዘጠኝ ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ አለመረጨቱን ጠቁመዋል።

ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካበቢዎች በየሦስት ዓመቱ አጎበር የሚቀየር ሲሆን ለ55 ወረዳዎች ቀደም ሲል የነበራቸው አጎበር ይተካላቸዋል ቢባልም እስካሁንየደረሳቸው መተማ፣ ገንደ ውሃ እና ፎገራ ወረዳዎች ብቻ ናቸው ተብሏል።

ወቅቱ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ በመሆኑ እስከ ታህሳስ 30 ድረስ በንቃት መሳተፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ወባን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ግንዛቤ የማጎልበት፤ የጤና ተቋማት ዝግጅትን ማሰደግ፤ የአጎበር ስርጭትን ማጠናከር እና የኬሚካል ርጭት በማከናወን ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የጤና ተቋማት በ2012 ካጋጠማቸው የግብዓት መቆራረጥ ወጥተው በቁሳቁስም ሆነ በባለሙያ ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል። ለዚህም ማንኛውም ትኩሳት ያለበትን ሰው ወደ ህክምና ተቋም ሲያመራ በመጀመሪያ የወባ ምርመራ እንዲደረግለት አቅጣጫ መቀመጡን አስተባባሪዋ ተናግረዋል።