አፍሪካ፡ ሩዋንዳ ለህክምና አገልግሎት ዕፀ ፋርስን ወደ ባህር ማዶ ለመላክ ወሰነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታትሟል
ሩዋንዳ ምጣኔ ሐብቷን ለማሳደግ በማለም ዕፀ ፋርስን ለሕክምና ተግባር ወደ ውጪ አገር ለመላክ ወሰነች።
ሰኞ ዕለት የተካሄደው የሚኒስትሮች ካቢኔ በሩዋንዳ ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ እፅዋትን ማልማት ስለመቻል እንዲሁም ለማቀነባበርና ወደ ባህር ማዶ ለመላክ የሚያስችል መምሪያ አጽድቋል።
የጤና ሚኒስትሩ ዳንኤል ንጋሚጄ ማክሰኞ ዕለት በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ለሕክምና ከሚውሉ ዕፅዋት መካከል ዕፀ ፋርስ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
አክለውም ሩዋንዳ " ለምርምር እና መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጥሬ እቃውን በማቅረብ አስተዋፅኦ እናደርጋለን፤ ገንዘብ ለማግኘት አቅደናል" ብለዋል።
ፈቃድ ያላቸው አምራቾች ብቻ በንግዱ ላይ እንደሚሳተፉ እንዲሁም በአገር ውስጥ ዕፀ ፋርስን መጠቀም ሕገወጥ ሆኖ እንደሚቀጥል የገለፀው ደግሞ የሩዋንዳ ዴቬሎፕመንት ቦርድ ነው።
ፈቃድ ሳይኖራቸው ዕፀ ፋርስን ወደ ማምረትና ሽያጭ የሚገቡ ግለሰቦች ከበድ ያለ ቅጣት ይጠብቃቸዋል የተባለ ሲሆን፣ ሲጠቀሙ መገኘትም የሁለት ዓመት እስር ያስከትላል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በመላው ዓለም ከዕፀ ፋርስ ሽያጭ 150 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የባርክሌይስ ባንክ መረጃ ያሳያል።













