የሊቨርፑሉ ሳዲዮ ማኔ በቫይረሱ በመያዙ እራሱን ለይቶ እያቆየ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ታትሟል
የሊቨርፑል እና የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጫዋቹ ሳዲዮ ማኔ በኮሮናቫይረስ መያዙን ክለቡ አረጋገጠ።
ይህንንም ተከትሎ ማኔ እራሱን ለይቶ እያቆየ እንደሚገኝ ክለቡ አስታውቋል።
የማኔ ኮቪድ-19 ውጤት የተሰማው አዲሱ የሊቨርፑል ፈራሚው ቲአጎ አልካንትራ በኮሮናቫይረሱ መያዙ ይፋ ከተደረገ ከሶስት ቀናት በኋላ ነው።
ማኔ "መለስተኛ የበሽታው ምልክት ከማሳየት ውጪ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛል" ሲል ሊቨርፑል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ማኔ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ሊቨርፑል ከአርሰናል በነበራቸው የፕሪሚየር ሊግ ፍልሚያ ለክለቡ ተሰልፎ ጎልም አስቆጥሮ እንደነበረ ይታወሳል።
ከሁለት ቀናት በፊት በተካሄደው እና ሊቨርፑል እና አርሰናል ባገናኘው የካራባኦ ካፕ ግጥሚያ ላይ ደግሞ ማኔ የሊቨርፑል ቡድን አባላት ውስጥ አልተካተተም ነበር።
ማኔ የመንግሥት ምክረ ሃሳብን በመከተል ከበሽታው እስኪያገግም ድረስ እራሱን ለይቶ ይቆያል ሲል ሊቨርፑል የእግር ኳስ ክለብ አስታውቋል።
በአዲሱ የውድድር ዘመን ለሊቨርፑል ሶስት ጊዜ ኳስን ከመረብ ማገናኘት የቻለው ሳዲዮ ማኔ በኮቪድ በመያዙ ምክንያት ቢያንስ አንድ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ያመልጠዋል ተብሏል።
ሰኞ ዕለት ፕሪሚየር ሊጉ በሊጉ የሚጫወቱ 10 ተጫዋቾች በቫይረሱ ተይዘዋል በማለት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።












