ዘረኝነት፡ ከፍተኛ ተቃውሞ ያጋጠመው የጋንዲ ሃውልት በማላዊ ቆመ

የማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የህንድ ዲፕሎማት

የፎቶው ባለመብት, Indian High Commission Malawi

ታትሟል

በህንዳውያኑ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና የነፃነት ታጋያቸው ማህተመ ጋንዲ ሃውልት በማላዊ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም ከሰሞኑ ቆሟል።

በጥቁር አፍሪካውያን ዘንድ ዘረኛ ነው የሚባለው የጋንዲ ሃውልት በጋና የተገረሰሰ ሲሆን በሌሎችም ቦታዎች ተቃውሞን አስነስቷል።

በማላዊም ቢሆን ለሁለት አመታትም ያህል ሃውልቱ መቆም የለበትም በሚል ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም በመዲናዋ ቆሟል።

በመጀመሪያ ታስቦ የነበረው ባላንትይር በምትባል ከተማ ሃውልቱን ለማቆም ነበር ።

ሃውልቱን ያቆመው የህንዱ ከፍተኛ ኮሚሽን ከሁለት አመተታት በፊት ለጋንዲ ሃውልት እሰራለሁ ሲል ጋንዲ መውደቅ አለበት (ጋንዲ መስት ፎል) በሚል እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

የህንዱ ነፃ አውጭ ለጥቁር አፍሪካውያን ከፍተኛ ንቀት የነበረውና በህይወት እያለም አፍሪካውያንን አፀያፊ ስድብ ይሳደብ ነበር በማለት ጉዳዩንም ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት ነበር።

ሆኖም በመዲናዋ ሊሎንግዌ ሃውልቱን ለማቆም እንዳሰቡ ተቃውሞ ይገጥመናል በማለትም ቀድመው አላሳወቁም ነበር።

ማላውያን ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም የህንድ ዲፕሎማቶች ቢሯቸውን ዘግተዋል።

በ78 አመቱ የተገደለው ጋንዲ ዛሬ የልደት ቀኑ ነው።

ሃውልቱ ሲቆም የማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይዘንሃወር ማካካ የተገኙ ሲሆን ጋንዲንም አሞግሰዋል።

"ማህተመ ጋንዲ ሰላማዊ በሆነ የትግል አካሄዱ ለህንድ ነፃነት ብቻ ሳይሆን ለአለም አቀፉም የቅኝ ግዛት ትግልም በርካታ አስተዋፅኦዎችን አበርክቷል" ብለዋል።

የጋንዲ ሃውልትን መቆም ከሚቃወሙት ጋንዲ መውደቅ አለበት (ጋንዲ መስት ፎል) እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች የተሰማ ምላሽ የለም።