ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጣልያን፡ የፓርላማ አባላቷን ቁጥር ለመቀነስ የህዝበ ውሳኔ ድጋፍ አገኘች
ጣልያን የፓርላማ አባላት ቁጥሯን ለመቀነስ ባደረገችው ህዝበ ውሳኔ ሁለት ሶስተኛው ህዝብ ድጋፉን ሰጥቷል።
ከ67 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የፓርላማ አባላቱ ቁጥር ይቀነስ የሚለውን የደገፈ መሆኑንንም በመንግሥት ቴሌቪዥን ራይ በሰራው ዳሰሳዊ ጥናት አመላክቷል።
በዚህም መሰረት የታችኛው ምክር ቤት አባላት ከ634 ወደ 400 የሚቀነስ ሲሆን የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላትም ቁጥር እንዲሁ እንዲቀነስ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ይህንን አጀንዳ በዋነኝነት ሲገፋ የነበረውም ፋይፍ ስታር ሙቭመንት የተባለውና ጣልያንን በጥምርነት የሚያስተዳድረው የመንግሥት አካል ነው።
አገሪቱ የምታወጣውን ወጪም ይቀንስላታል በማለትም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ውሳኔውም በአጠቃላይም የጣልያን የፓርላማ አባላትና ሴናተሮችን ቁጥር ከ945 ወደ 600 ዝቅ ያደርገዋልም ተብሏል።
በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩ ወደ ፓርላማ የተወሰደ ሲሆን የህገ መንግሥት መሻሻል ስለሚያስፈልገው ነበር የህዝበ ውሳኔ ድጋፍ ያስፈለገው።
ይሄም የህገ መንግሥት ማሻሻያም ጣልያን ከሁለት አመት በኋላ ልታደርገው ካቀደችው አገራዊ ምርጫ በፊት መከናወን አለበት።
በሲኒየር ስታር ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉይጂ ዲ ማዮ ውጤቱን "ታሪካዊ" ብለውታል።
"መካከለኛ የሆነ ፓርላማ ሊኖረን ይገባል፤ ከ300 በላይ መቀነሱም ትልቅ ድል ነው" ብለውታል።
አገሪቷ የፓርላማ አባላቷን ቁጥር ብትቀንስ በአስር አመታት ውስጥ ከ 1 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ ያድናታልም በማለት ፋይቭ ስታር ሲሟገት ነበር።
ሆኖም ተችዎች ዲሞክራሲኝ ያዳክማል እያሉ ነው።
ህዝበ ውሳኔው ከክልላዊ ምርጫዎች ጎን ለጎንም ተካሂዷል።