ኮሮናቫይረስ፡ በግሪክ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በኮቪድ-19 ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በግሪኳ ደሴት ሌስቦስ በሚገኘው ጊዜያዊ የስደተኞች ማቆያ ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ።
በኬራ ቴፔ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ሰባት ሺ የሚሆኑ ስደተኞች በተደረገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከ240 በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጧል ተብሏል።
በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት በሞሪያ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያጋጠመውን የእሳት አደጋ ተከትሎ ነው አዲሶቹ ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያዎች እንዲቋቋሙ የተደረጉት።
በእሳት አደጋው 12 ሺ የሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤት አልባ ሆነዋል።
አራት አፍጋኒስታናውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች መስከረም 8 ላይ እሳቱን በማስነሳት ተከስሰዋል። የግሪክ መንግሥት እንዳስታወቀው ግለሰቦቹ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በማዕከሉ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመቃወም ነው እሳቱን ያስነሱት ብለዋል።
ዛሬ ሰኞ ዕለት ደግሞ የመንግስት ቃል አቀባይ እንዳረጋገጡት 243 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ለመያዛቸው ምክንያቱ ደግሞ ከሞሪያ ማቆያ ወጥተው በጊዜያዊ መጠለያ እንዲቆዩ በመደረጋቸው ነው ተብሏል።
ቃል አቀባዩ አቀብለውም በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠው ሰዎች አማካይ የእድሜ ጣሪያ 24 ሲሆን አብዛኛዎቹ ደግሞ የቫይረሱን ምልክት የማያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በአስርታት የሚቆጠሩ ፖሊሶችና የጊዜያዊ ማዕከሉ ሰራተኞችም ጭምር ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን በቫይረሱ አለመያዛቸው ተረጋግጧል።
በሞሪያ የእሳት አደጋው ከማጋጠሙ ሁለት ሳምንታት በፊት ወደ 9 ሺ የሚጠጉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ደሴቲቱ እንዲዘዋወሩ ተደርገው ነበር። እሳቱን ሸሸተው ከሄዱት መካካል አብዛኛዎቹ ደግሞ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩና ምግብና ውሃ ማግኘት የሚቸገሩ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግሪክ የስደተኞች ሚኒስትሩ ኖቲስ ሚታራቺ እንዳሉት ለእሳቱ መነሳት ምክንያት የሆኑት ግለሰቦች ቅጣታቸውን ጨርሰው ወደመጡበት አገር እንዲመለሱ ይደረጋሉ።














