ፓናማ ውስጥ ከኃይማኖት ጋር የተያያዘ ጅምላ መቃብር ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Panama Public Prosecutor
የፓናማ ፖሊስ ከአንድ ኃይማኖት ጋር ግንኙነት አለው ያለውን የጅምላ መቃብር ማግኘታቸውን አስታወቀ።
ፖሊስ ምርመራ ላይ እንደሆነ ጨምሮ አስታውቋል።
መርማሪዎች በሰሜን ምዕራብ የፓናማ አውራጃ ከተገኘው የጅምላ መቃብሩ የተቆፈሩ አፅሞችን እየሰበሰቡ ነው።
ባለፈው ጥር አሁን የጅምላ መቃብሩ ከተገኘበት ሥፍራ ብዙም ሳይርቅ የሰባት ሰዎች አስከሬን አንድ ላይ ተቀብሮ መገኘቱ ይታወሳል።
ሬሳዎቹ አንድ ሰይጣን ለማውጣት ጉልበት የተቀላቀለበት ኃይል ከሚጠቀም ኃይማኖት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሏል።
አቃቤ ሕግ አዛኤል ቱግሪ፤ መርማሪዎች በተራራዎች መካከል 10 ሰዓት ያክል ተጉዘው የጅምላ መቃብሩን እንዳገኙት ያስረዳሉ።
መቃብሩ ንጋቤ ቡግሌ የተሰኘ ሥፍራ ካለ አንድ ወንዝ አቅራቢያ ነው የተገኘው።
የጅምላ መቃብሩ ከፓናማ ዋና ከተማ ፓናማ ሲቲ 350 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው የሚገኘው።
አቃቤ ሕጉ በአሁን ወቅት የአስከሬን ቁጥርና ፆታ መለየት እጅግ አዳጋች ነው ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
አፅሞቹ ተሰብስበው የሬሳ ምርመራ እንደሚደርግላቸው ታውቋል።
ከቀናት በፊት ፖሊስ የኒው ላይት ኦፍ ጋድ ቤተ እምነት መሪ ነው የተባለ ሰው ወርሃ ጥር ላይ ከተገኘው መቃብር ጋር በተያያዘ ክስ በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ባፈለው ጥር የጅምላ መቃብሩ የተገኘው ሶስት ሰዎች አምልጠው በአቅራቢያው ወዳለ ሆስፒታል ሄደው ጥቆማ ከሰጡ በኋላ ነው።
መቃብሩ ሲቆፈር አንዲት ነብሰ ጡር እናትና አምስት ልጆቿ እንዲሁም አንድ ታዳጊ ተገኝተዋል።
ይህን ተከትሎ ፖሊስ ባካሄደው ፍተሻ በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ አንዲት እርቃኗን ያለች ሴት፣ ገጀራዎች፣ ቢላዎች መስዋዕት የሆነ ፍየል አግኝቷል።
ቤተ እምነቱ ሰይጣን ለማውጣት በሚል ኃይል የተቀላቀለበት መንገድ ይጠቀም ነበር ተብሏል።
በኃይማኖቱ ቁጥጥር ሥር የነበሩ 15 ሰዎች መለቀቃቸውም በጊዜው ተዘግቦ ነበር።












