ኮሮናቫይረስ፡ በፈረንሳይ በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ አለፈ

ጭምብል ያጠለቀች ግለሰብ በፈረንሳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ፈረንሳይ በአንድ ቀን ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር የመዘገበች ሲሆን ተቆጣጠርኩት ስትል እንደገና ያገረሸውን ወረርሽኝ ለመግታት እየታገለች ነው።

የአገሪቷ የጤና ባለሥልጣናት ቅዳሜ ዕለት 10 ሺህ 561 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ አርብ ዕለት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ100 ጭማሬ አሳይቷል።

ሆስፒታል የሚገቡና ፅኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑ ተነግሯል። ያገረሸውን ወረርሽኝን ተከትሎም ሕዝቡ መሰባሰብን እንዲያቆም የሐኪሞች ቡድን አሳስቧል።

ፈረንሳይ ቫይረሱ እንደገና ካገረሸባቸው የአውሮፓ አገራት አንዷ ናት።

በአህጉሩ ያሉ አገራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መጋቢት ወር ላይ ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ያላሉ ሲሆን፤ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሰኔ ወር ላይ ጀምሮ ቀስ በቀስ እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ወር ደግሞ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል።

በአገሪቷ ቅዳሜ እለት 2 ሺህ 432 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፤ አርብ ዕለት ከነበረው በ75 ጨምሯል። ከእነዚህ መካከልም 417ቱ ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ገብተዋል። ይህ ቁጥርም አርብ ዕለት ከነበረው በ28 ብልጫ አሳይቷል።

የ17 ሰዎች ሕይወትም አልፏል።

ፈረንሳይ ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በዓለም ካሉ አገራትም በሟቾች ቁጥር ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኮሮና