ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስፔን ቄሶችን የገደለው የቀድሞ ኮሎኔል 133 አመት እስር ተፈረደበት
የስፔን ፍርድ ቤት የኤል ሳልቫዶር ጦር ይመራ የነበረ የቀድሞ ኮሎኔል አምስት ቄሶችን በመግደል ወንጀል የ133 አመት እስራት ወስኖበታል።
ግድያው የተፈፀመው በኤል ሳልቫዶር በጎርጎሳውያኑ 1989 ነው።
የቀድሞው ኮሎኔል ኢኖሴንቴ ኦርላንዶ ሞንታኖ በአሁኑ ወቅት የ77 አመት እድሜ ባለፀጋ ሲሆን "በሽብርተኝነት ግድያ" በሚልም ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
በኤልሳልቫዶር የርስበርስ ጦርነት ወቅት የካቶሊክ ቄሶች ከግራ ቀኝ ዘመም ታጣቂዎች ጋር ይወግናሉ በሚል ይወነጀሉም ነበር።
አሜሪካ አሳልፋ የሰጠችው ኢኖሴንቴ ምንም ወንጀል አልፈፀምኩም ሲል ክዷል።
የስፔን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞውን ኮሎኔል በአጠቃላይ ስምንት ሰዎችን በመግደል ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።
ሆኖም የቄሶቹ የቤት ጠባቂ፣ ታዳጊ ልጇና ሌላኛው ስድስተኛው የጀሱትስ ቄስ ግድያ ተጠያቂ አይሆንም ተብሏል።
ምክንያቱም አሜሪካ አሳልፋ ስትሰጠው ለአምስቱ ቄሶች ግድያ ክስ ነው።
በተሽከርካሪ ወንበር እርዳታ የመጣው የቀድሞው ኮሎኔል ለእያንዳንዱ ግድያ ክስም 26 አመት፣ ስምንት ወርና አንድ ቀን በእስር እንዲያሳልፍ መወሰኑን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል በዘገባው አስነብቧል።
በፍርድ ቤቱ በርም ጠበቃ ማኑኤል ኦሌ ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት በግድያው የተጎዱ ቤተሰቦች በብያኔው መደሰታቸውን ነው።
"የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚያሳየው ግድያው በኤል ሳልቫዶር ከፍተኛ የጦር ትእዛዝ መሰረት ታቅዶና ሆን ብሎ እንደተፈፀመ ነው" ብለዋል።
የቀድሞው ኮሎኔል ውሳኔውን ይግባኝ መጠየቅ ይችላሉ ተብሏል።
ስለ ግድያው ምን እናውቃለን?
ግድያው የተፈፀመው በወታደራዊው መንግሥትና የግራ ቀኝ ታጣቂው ፋናቡንዶ ማርቲ ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር መካከል ከጎርጎሳውያኑ 1979-1992 በነበረው ጊዜ ነው።
በዚህ ወቅት ከተገደሉት ቄሶች መካከል አንዱ ኢግናሲዮ ኤላኩሪያ የሚባሉ ሲሆን በኤል ሳልቫዶር የሚገኘውም የሴንትራል አሜሪካን ዩኒቨርስቲ ኃላፊ ነበሩ። በተጨማሪም በነፃነት እንቅስቃሴዎች ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ነበሩ።
ቄሶቹና ሁለቱ ሴቶችን ከአልጋቸው አውርደው እየጎተቱ ከወሰዷቸው በኋላ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ ገደሏቸው።
አቃቤ ህግ እንደሚለው ኢኖሶንቴ በወቅቱ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር የነበረ ሲሆን በወቅቱ ለተፈፀሙ በርካታ ግድያዎች ጥፋተኛ ነበር።
እንዲሁም ከግራ ክንፉ ብሄራዊ ነፃ አውጭው ግንባርም የነበሩ የሰላም ስምምነቶችን ይቃወም ነበር ተብሏል።
የቀድሞው ምክትል መከላከያ ሚኒስትርም የጀሱትስ ቄሶች እንዲገደል ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ቄሶቹ ላይ በቀጥታ የተኮሱት የቀድሞ ሌተናንት ሬኔ ዩሺ ሜንዶዛ በአቃቤ ህግ ምስክርነት ቀርቧል።
ስፔን እንዴት መጣ?
የቀድሞው ኮሎኔል ወደ አሜሪካ በጎርጎሳውያኑ 2002 ሲሆን የሄደው ከኢሚግሬሸን ማጭበርበር ጋር ተያይዞ በእስር ላይ የነበረ ሲሆን ስፔንም ተላልፈው እንዲሰጧት ጠየቀች።
አሜሪካ ከሶስት አመት በፊት አሳልፋ ሰጠቸው። እሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የኤል ሳልቫዶር ባለስልጣናትም ከ1989 ግድያ ጋር ክስ ቢመሰረትባቸው ኤል ሳልቫዶር አሳልፌ አልሰጥም ብላለች።