ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አለም አቀፉ ማህበረሰብ ቢማፀናትም ኢራን ተፋላሚው ናቪድ አፍካሪን በሞት ቀጣች
አለም አቀፉ ማህበረሰብ ቢማፀናትም ኢራን አሻፈረኝ ብላ ሰው ገድሏል ያለችውን ተፋላሚ በሞት ቀጥታለች።
በሞት የተቀጣው ተፋላሚ ናቪድ አፍካሪ ይባላል፤ እድሜውም 27 ነው።
ከሁለት አመት በፊት በነበረው መንግሥታዊ ተቃውሞ ላይ አንድ ጥበቃን ገድሏል ተብሏል።
ናቪድ ግን እንዲናዘዝ ከፍተኛ ድብደባና እንግልት እንደተፈፀመበት ተናግሯል።
የተፋላሚውን የሞት ቅጣት አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ "ፍትህ የተዋረዳባት" ብሎታል።
ተደብቆ በምስጢር ከእስር ቤት የወጣ የናቪድ ድምፅም "ከሞትኩኝ እንድታውቁት የምፈልገው ወንጀሉን እንዳልፈፀምኩ ነው። ንፁህ ሰው ነኝ። ባለ በሌለለኝ አቅም ንፁህነቴን ለማስረዳት ብታገልም በመጨረሻም የሞት ፍርድ እንዲፈረድብኝ ሆኗል " ብሏል
ናቪድ በደቡቧ ሺራዝ ግዛት ስቅላት እንደተፈፀመበት የሃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።
ከመሞቱ በፊት ቤተሰቡን ማየት እንዳልቻለም ጠበቃው ተነግሯል፤ ይህም የኢራንን ህግ የጣሰ ነው ተብሏል።
"ሞቱን ለማፋጠን በሚል እንዴት ቤተሰቦቹን ለመጨረሻ ጊዜ እንዳያይና እንዳይሰናበት አደረጋችሁት" በማለትም ሃሰን ዩኔሲ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
የሞቱ ቅጣቱ ተፈፃሚ እንዳይሆንበትም በርካታቶች የኢራንን መንግሥት ተማፅነዋል። ከነዚህም ውስጥ 85 ሺ አባላት ያሉበት አለም አቀፉ የአትሌቶች ማህበር ይገኝበታል።
አለም አቀፉ የስፖርት አስተዳደር ማህበርም ተፋላሚው በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በመሳተፉ በኢፍትሃዊነት ኢላማ እንደተደረገና የሞት ቅጣቱን ተግባራዊ የምታደርገው ከሆነ ኢራን ከአለም አቀፉ ስፖርት እንድትገለልም ጥሪ አቅርቧል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲሁ ምህረት እንዲደረግለት የጠየቁ ሲሆን የተፋላሚው ብቸኛ ወንጀልም መንግሥትን ተቃውሞ ሰልፍ ላይ መውጣቱ ነው ብለዋል።
የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ግድያውን የሚያሳዝን ነው ያለ ሲሆን ለቤተሰቦቹና ጓደኞቹም መፅናናትን ተመኝቷል።
"በአለም ላይ ያሉ አትሌቶች በሙሉ ህይወቱ እንድትተርፍ ብንማፀንም ችላ ብለው መግደላቸው በጣም የሚያስከፋና የሚያሳዝን ነው" ብሏል መግለጫው።
ከሁለት አመት በፊት የነበረው ተቃውሞ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫናንና ፖለቲካዊ ጭቆናን በመቃወም ነበር በርካቶች ጎዳና ላይ የወጡት
የናቪድ ወንድሞች ቫሂድና ሃቢብ ወንድማቸው የሞት ቅጣት በተፈረደበት ክስ የ54ና የ27 አመት እስር እንደተፈረደባቸውም የኢራን ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ገልፀዋል።
ከእስር ቤት ተደብቆ በሚስጥር ወጣ የተባለው የናቪድ ድምፅም ላይ ክፉኛ እንዳንገላቱትና እንደደበደቡት ገልጿል።
እናቱም ልጆቿ እርስ በርስ ምስክር እንዲሆኑ ተገደዋል ብላለች።
በርካታ የኢራን ሚዲያዎች ናቪድ ጥበቃን ሲገድል የሚያሳይ ቪዲዮ አለ ብለው ሪፖርት ቢያደርጉም ምንም ነገር እንደሌለ ጠበቃው በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
እንደ ማስረጃነት የቀረበው ቪዲዮም ከግድያው አንድ ሰዓት በፊት የተቀረፀ መሆኑን ነው። የኢራን ባለስልጣን በበኩላቸው ናቪድ ድብደባም ሆነ እንግልት አልደረሰበትም ብለዋል።
ናቪድ በፍልሚያ የብሄራዊ ሻምፒዮንነትን ስፍራ ጨብጧል። ስፖርቱ በኢራን ታሪካዊ ሲሆን ከፍተኛ ተወዳጅነትም አለው።