ለትራምፕ ድጋፍ ለማድረግ ሐይቅ ላይ ሰልፍ የወጡ ጀልባዎች ሰጠሙ

ታትሟል

በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት በመጪው ኅዳር በሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ዶናልድ ትራምፕን እንደግፋለን ብለው ጀልባዎቻቸውን ይዘው ሐይቅ ላይ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሰጥመዋል።

የግዛቲቱ ባለሥልጣናት ወጀቡ የተነሳው በርካታ ጀልባዎች አንድ ላይ በመቅዘፋቸው ምክንያት ነው ይላሉ።

አደጋው የደረሰው ትራቪስ የተሰኘ የቴክሳስ ግዛት ዋና ከተማ ኦስቲን አጠገብ የሚገኝ ሐይቅ ላይ ነው።

ከሥፍራው የተገኙ ምስሎች የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ መለያ ባንዲራን ሲያውለበልቡ የነበሩ ጀልባዎች እርስ በርስ ሲገጫጩ ያሳያሉ።

መገናኛ ብዙሃን እስካሁን ድረስ የተመዘገበ አደጋ ባይኖርም በርካቶችን የማዳን ሥራ ሲከናወን ነበር ሲሉ ዘግበዋል።

የትራቪስ ሐይቅ ለትራምፕ ድጋፍ የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ሰልፍ ፌስቡክ ላይ በተነገረ አዋጅ የታቀደ ሲሆን ቢያንስ 2 ሺህ 600 ሰዎች እንመጣለን ሲሉ አሳውቀው ነበር።

የጀልባውን ሰልፍ ያዘጋጁት የትራቪስ ክፍለ ግዛት የትራምፕ ደጋፊ አባላት ናቸው ተብሏል።

ሐይቁ ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚመረምር ቡድን ወደ ሥፍራው ተልኳል። ጉዳቱ የደረሰው በተፈጥሮ ምክንያት እንጂ በሰው እጅ አለመሆኑን ደርሰንበታል ይላሉ የትራቪስ ክፍለ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ክሪስተን ዳርክ።

“በርካታ ጀልባዎች አደጋ ላይ ነን ብለው ሲደውሉልን ወደ ሥፍራው በፍጥነት መጥተናል” ብለዋል ቃል አቀባይዋ።

ቃል አባይዋ እንደሚሉት ሐይቁ ላይ መሰብሰብ ከነበረባቸው በላይ ጀልባዎች ተሰብስበው አንድ ላይ ሲቀዝፉ ነው ወጀብ እንዲነሳ የሆነው።

የአየር ሁኔታ ትንበያ ሰዎች በሥፍራው ማዕበል ሊያስነሳ የሚችል ምንም ዓይነት የአየር ፀባይ እንዳልነበረ ተናግረዋል።

አደጋው የደረሰው ቅዳሜ አመሻሹን በግዛቲቱ ሰዓት አቆጣጠር መሠረት 11 ሰዓት አካባቢ ነው።

የሰልፉ አዘጋጆች ለአሽከርካሪዎች ጀልባዎቻቸውን ከ16 ኪሎ ሜትር በሰዓት በላይ እንዳይሽከረክሩ ትዕዛዝ ሰጥተናል ይላሉ።

አሜሪካ ቅዳሜና እሁድ የሠራተኞች ቀን እያከበረች ትገኛለች።

በመጪው ወርሃ ኅዳር የሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ፕሬዝደንት ትራምፕንና የዴሞክራት ፓርቲ ዕጩው ጆ ባይደንን ያፋልማል።