በጀርመን አምስት ህፃናት በአፓርትመንት ውስጥ ሞተው ተገኙ

ህፃናቱ የተገኙበት አፓርትመንት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በምዕራብ ጀርመኗ ሶሊንገን ከተማ በሚገኝ አፓርትመንት ውስጥ አምስት ህፃናት ሞተው እንደተገኙ ፖሊስ አስታውቋል።

ሃሳዴላ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሚገኘው አፓርትመንት ነዋሪዎች ድንገተኛ ጥሪ አድርገው ፖሊስ እንደደረሰም ተገልጿል።

ህፃናቱን በመግደል የተጠረጠረችው የህፃናቱ እናት ራሷን በባቡር ጣቢያ ልታጠፋ ሞክራ ነበር። ግለሰቧ 27 አመት እንደሚሆናትም ተዘግቧል።

ህፃናቱ በምን መንገድ እንደሞቱ ፖሊስ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ቢልድ የተባለው የጀርመን ድረ ገፅ በበኩሉ ባሳተመው መረጃ አምስቱ ህፃናት እድሜያቸው ከአንድ- እስከ ስምንት አመት የሚሆናቸው ናቸው ብሏል።

የ11 አመቱ ስድስተኛው ልጅ ጉዳት ቢደርስበትም ተርፏል።

ፖሊስ ስለ ህፃናቱ ወላጆች ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም እናታቸው ራሷን ለማጥፋት ባቡር ፊት ላይ ብትወድቅም ተርፋለች ተብሏል።

በአሁኑ ሰዓትም ላይ በሆስፒታል ውስጥ ህክምና ላይ ትገኛለች።

በአካባቢው የሚገኝ ፖሊስ ቃለ አቀባይ ለቢልድ እንደተናገሩት "ምክንያቷ ምንድን ነው የሚለውን እስካሁን አላወቅንም። እናቲቱን መጠየቅ እንዲሁም መመርመር አለብን" ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት የአፓርትመንቱ መግቢያ የተዘጋ ሲሆን የፖሊስ መኪናና አምቡላንስ በአካቢው እንደሚታይም ተገልጿል።