ሳዑዲ አራቢያ፡ በሁለተኛው ዙር 'የፀረ-ሙስና ዘመቻ' ንጉሡ የመከላከያ ኃላፊዎችን ከሥልጣን አነሱ

የሳዑዲ ንጉሥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሁለት የሳዑዲ ንጉሣዊ ቤተሰቦችን ጨምሮ ሌሎችም ብዙ ባለሥልጣኖች ከኃላፊነታቸው ተነሱ።

የሳዑዲው ንጉሥ ሰልማን፤ ልዑል ፋሀድ ቢን ተርኪን ከሥልጣን አንስተዋል። ልዑሉ በሳዑዲ እየተመራ በየመን የሚንቀሳቀሰው ኃይል ኮማንደር ነበር።

ልጁ አብዱላዚዝ ቢን ፋሀድም ከምክትል አገረ ገዢነት ተነስቷል።

እነዚህና ሌሎች አራት ባለሥልጣኖች በመከላከያ ሚንስትር ሳሉ ያካሄዱት “አጠራጣሪ የገንዘብ ዝውውር” ላይ ምርመራ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የንጉሡ ልጅ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን በመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድ የተንሰራፋውን ሙስና የማስወገድ ዘመቻ ላይ ናቸው።

ተቺዎች እንደሚሉት ግን አልጋ ወራሹ ሥልጣናቸውን ሊገዳደሩ የሚችሉ ሰዎችን ከኃላፊነት እያስወገዱ ነው።

በዓመቱ መባቻ ዋል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፤ የንጉሡን ታናሽ ወንድም ልዑል አህመድ ቢን አብዱላዚዝ እና የቀድሞው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ናይፍ ጨምሮ ሦስት ከፍተኛ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ታስረዋል።

ከአራት ዓመት በፊት በርካታ የሳዑዲ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት፣ ሚንስትሮችና ነጋዴዎች ሪያድ በሚገኘው በሪትዝ ካርልተን ሆቴል ታግተው ነበር።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ እና የሳዑዲ ዜግነት ያላቸው ቢሊየነሩ ሼህ ሞሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲ ታስረው እንደነበርም ይታወሳል።

ኋላ ላይ አብዛኞቹ 106.7 ቢሊዮን ዶላር ለሳዑዲ ለመክፈል ከተስማማሙ በኋላ ተለቀዋል።

የ35 ዓመቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢል ሰልማን፤ እጅግ ወግ አጥባቂ አገሩ ላይ ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት ለውጥ እንደሚያደርጉ ቃል ከገቡ በኋላ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አወድሷቸዋል።

ሆኖም ግን ከጋዜጠኛው ጀማል ካሾግጂ ግድያ እንዲሆም ከቀድሞው የሳዑዲ ሰላይ ገድያ ጋር በተያያዘ ስማቸው ይብጠለጠላል። ከየመን ጋር ባለው ግጭትም ይተቻሉ።

በአገሪቱ ሴቶች ላይ በሚደርሰው ጫና ልዑል አልጋ ወራሹን በርካቶች ይወቅሷቸዋል። ምንም እንኳን ሴቶች መኪና እንዳይነዱ የሚከለክለውን ሕግ ቢሽሩም፤ ሳዑዲ የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ ረገድ ብዙ ይቀራታል።