ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ ባለ አምስት ፎቅ ሕንጻ ተደርምሶ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 18 ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ
በምዕራብ ሕንድ ሰኞ ዕለት ባለ አምስት ፎቅ ሕንጻ ተደርምሶ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 18 ሰዎች ደግሞ አሁንም በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ ተገለፀ።
ሕንጻው የሚገኘው ከሙምባይ 170 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ማሃድ ከተማ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን 47 ክፍሎች እንዳሉትም ፖሊስ አስታውቋል።
እስካሁን ድረስ ከፍርስራሹ ውስጥ የ60 ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ መቻሉን የአካባቢው አስተዳዳር ለአገር ውስጥ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በሕንድ በዝናብ እና ከባድ አውሎ ነፋስ ወቅት የሕንጻ መደርመስ መከሰት የተለመደ ነው።
ሕንጻው ሰኞ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ መደርመሱን ፖሊስ በሪፖርቱ አመልክቷል።
አደጋውን አሳዛኝ ያሉት የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አሚት ሻህ የአገሪቱ የአደጋ ስጋት መከላከል ኃይል "የሚቻለውን ሁሉ ምላሽ እንዲሰጥ" አዘዋል።
የሕይወት አድን ሠራተኞች ከፍርስራሶቹ ውስጥ በህይወት የሚገኙ ሰዎችን ለማውጣት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
ሕንጻው ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 10 ዓመት እንደሆነው እየተነገረ ነው።
በሕንጻው ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከመደርመሱ በፊት ይንቀጠቀጥ እንደነበር ገልፀው በፍጥነት በመውጣት መትረፋቸውን ገልፀዋል።
የዓይን ምስክሮች ደግሞ ለመገናኛ ብዙኀን እንደተናገሩት ሕንጻው ሲደረመስ ከፍተኛ ደምጽ ተሰምቶ ነበር። ከፍርስራሹ ውስጥ ጭስ ሲመለከቱ ወደ ስፍራው በፍጥነት በመጓዝ መድረሳቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
ከሕንጻው ስርየተቀበሩ ሰዎች የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰሙ መስማታቸውን የሚናገሩት የአይን ምስክሮቹ፣ ከዚኣ በኋላ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ጋር በመደወል በፍጥነት የነፍስ ማዳን ስራው እንዲጀመር ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
በዚህ ዓመት በሕንድ ውስጥ በከባድ ዝናብ 800 ያህል ሰዎች መሞታቸውን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘገባ ያሳያል።