እግር ኳስ፡ ሮናልዲንሆ በፓራጓይ በቅንጡ ሆቴል 'ከታሰረ' በኋላ ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, ASUNCION COURTHOUSE/EPA
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ ሮናልዲንሆ ዲ አሲስ ሞሬራ፣ (በቅጽል ስሙ ጎቾ) በፓራጓይ ላለፉት 5 ወራት በእስር ላይ ነበር፤ በቁም እስር፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ሐሰተኛ ፓስፖርት ይዞ በመገኘቱ ነው፡፡
ሮናልዲንሆ ከወንድሙ ጋር በመጓዝ ላይ ሳለ ነበር በፓራጓይ የተጭበረበረ ፓስፖርት አሳይቶ ለማለፍ ሲል በሕግ አስከባሪዎች የተያዘው፡፡
የዓለም ዋንጫን ለአገሩ በማስገኘትና አንጸባራቂ የኳስ ዘመን በማሳለፍ ዓለም የሚያውቀው ሮናልዲንሆ ለአንድ ወር ያህል ብቻ ነው እስር ቤት የቆየው፡፡
ከዚያ በኋላ ግን የዋስ መብቱ ስለተከበረለት አራቱን ወራት በቁም እስር ላይ ነበር የቆየው፡፡ የቁም እስሩም በፓራጓይ ዋና ከተማ አሱንሲዮን በሚገኝ ደልቃቃ ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡
ወንድማማቾቹ አሁን የተለቀቁት 200ሺህ የአሜሪካን ዶላር በቅጣት ለመክፈል ከተስማሙ በኋላ ነው፡፡
ሮናልዲንሆ በ2015 ጫማውን በድንገት ከመስቀሉ በፊት በእግር ኳስ ሕይወቱ አጭር ግን እጅግ ስኬታማ የሚባል ጊዜን አሳልፏል፡፡
ጎቾ አገሩ ብራዚል ለ5ኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫ እንድታነሳ ከማድረጉም ባሻገር ከስፔኑ ባርሴሎና ጋር ሻምፒዮንስ ሊግን እና ላሊጋን ድል አድርጓል፡፡
ከዚያ በኋላም በፓሪስ ሴን ዣርማን እንዲሁም በሚላን እግር ኳስ ቡድኖች የማይዘነጉ ጊዜዎችን አሳልፏል፡፡
ባለፈው መጋቢት እሱና ወንድሙ ሮቤርቶ ዴ አሲስ ሞሬራ ፓራጓይ በተጭበረበረ ፓስፖርት ሲገቡ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡ ወንድሙ ሮቤርቶ የሮናልዲንሆ የቢዝነስ ጉዳዮች ሥራ አስኪያጁ ሆኖ ይሰራል፡፡
ሮናልዲንሆ ወደ ፓራጓይ ያቀናው ለተቸገሩ ሕጻናት ገንዘብ ለማሰባሰብ ነበር፡፡
ሆኖም ፓስፖርቱ ሐሰተኛ በመሆኑ 40ኛ ዓመቱን እስር ቤት ለማክበር ተገዷል፡፡
የዋስ መብቱን ካስከበረ በኋላ ቆይታ ያደረገው ግን በቅንጡ ሆቴል ውስጥ ነበር ተብሏል፡፡
አቃቢ ሕግ ሮናልዲንሆነ ሐሰተኛ ፓስፖርት ስለመያዙ ላያውቅ ይችላል፣ ነገር ግን ወንድሙ ይህን ያውቅ ነበር ብሏል፡፡
ሁለቱ ወንድማማቾች ለኡራጓይ ፍርድ ቤት ክሱን አስተባብለዋል፡፡














