ቻምፒየንስ ሊግ፡ ኔይማር ያነባበት፤ ሌዋንዶውስኪ የፈነደቀበት ምሽት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀርመኑ ባየርን ሚዩኒክ የፈረንሳዩን ፒኤስጂ በመርታት የኮሮናቫይረስ ዘመን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ባለድል ሆኗል።
የቀድሞው የፒኤስጂ ተጫዋች ኪንግስሊ ኮማን በ59ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ነው የጀርመኑ ክለብ በአውሮፓ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን ዋንጫ ለስድስተኛ ጊዜ ያነሳው።
ባለፈው ኅዳር ወር ባየርን ሚዩኒክን በጊዜያዊነት የተረከቡት አሠልጣኝ ሃንስ ፍሊክ የጀርመን ቡንደስሊጋን ማንሳታቸው አይዘነጋም። አሁን ደግሞ የሥራ ማመልከቻቸው ላይ ቻምፒየንስ ሊግ ጨምረዋል።
የፒኤስጂ የፈት መስመር አሸከርካሪዎች ብራዚላዊው ኔይማርና ፈረንሳዊው ወጣት ምባፔ በሃዘን አንገታቸውን ደፍተው ታይተዋል።
የጨዋታው ኮከብ የነበረው የባየርን ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኑዌር ኔይማርና ምባፔን አላነቃንቅ ብሎ አምሽቷል።
ሁለቱ ቡድኖች ተፈራርተው የገቡበት ጨዋታው የታሰበውን ያክል አዝናኝና ጎል የተመረተበት ባይሆንም ባየርን ሚዩኒክ የተሻለ ቡድን ሆኖ አምሽቷል።
የፒኤስጂው ምባፔ በባየርን የጎል ሳጥን ውስጥ በጆሽዋ ኪሚክ ተጠልፎ የወደቀ ቢመስልም የዕለቱ ዳኛ ጥፋቱ ፍፁም ቅጣት ምት የሚያሰጥ አይደለም ብለዋል።
ጎል በማምረት የሚታወቁት ባየርኖች የተከላካይ መስመራቸው የሳሳ በመሆኑ በፒኤስጂ ከዋክብት ጉድ ይሆናሉ ተብሎ ቢገመትም ኔይማርና ምባፔ እንዲሁም ዲ ማሪያ ልዩነት መፍጠር አልቻሉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢቫን ፔሪሲች ምትክ ኮማንን ያሰለፉት ሃንስ ፍሊክ ከስፖርት አዋቂዎች ምስጋና ተችሯቸዋል።
ባየርን ሚዩኒክ ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ዋንጫው በማንሳት ታሪክ ከመሥራታቸው አልፎ የስፔንና አውሮፓ ኃያሉን ባርሴሎና በሩብ ፍፃሜው 8-2 በመርታት ብዙዎችን አጀብ አሰኝተዋል።
ረብጣ ሚሊዮን ዶላሮች ተጫዋቾች ላይ ያፈሰሰው ፒኤስጂ ለሚቋምጥለት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ፍፃሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢደርስም ውጤታማ አልሆነም።
ባየርን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ስድስት ጊዜ በማንሳት ከሊቨርፑል ጋር እኩል ተቀምጧል። ዋንጫውን ሪያል ማድሪድ 17 ጊዜ በማንሳት አንደኛ ሲሆን ኤሲ ሚላን 7 ጊዜ በማንሳት ሁለተኛ ነው።














