ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በሕንድ ዴልሂ በኮቪድ-19 ከተጠቁት መካከል የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው
በሕንድ ዋና ከተማ ከወንዶች በበለጠ ሴቶች በኮቪድ-19 መጠቃታቸውን በከተማዋ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ የአንቲቦዲ ምርመራ አረጋገጠ።
መንግሥት ባካሄደው በዚህ የዳሰሳ ጥናት የደም ናሙና ምርመራ ከተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የኮቪድ-19 አንቲቦዲ አዳብረው ተገኝተዋል።
የመጀመሪያው የዳሰሳ ጥናት የተካሄደው በሐምሌ ወር ሲሆን ወደ 23.48 በመቶ ያህል የከተማዋ ነዋሪዎች የኮሮናቫይረስ አንቲቦዲ አዳብረው መገኘታቸውን ተረጋግጦ ነበር።
በሕንድ ዴልሂ እስካሁን ድረስ 150 ሺህ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል 4,257 ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በቅርብ ጊዜ የተደረገው የዳሰሳ ጥናት የተካሄደው በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ሲሆን፣ በከተማዋ ከሚኖሩና ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል 32.2 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ለኮሮናቫይረስ አንቲቦዲ አዳብረው ተገኝተዋል።
በአንጻሩ ወንዶች ደግሞ 28.3 በመቶ ያህሉ የኮሮናቫይረስ አንቲቦዲ ማዳበራቸው ተገልጿል።
ለዚህ ምከንያቱ ምን ይሆናል ለሚለው ጥያቄ እስካሁን መልስ አልተገኘም።
በአጠቃላይ ምርመራ ከተደረገላቸው የዴልሂ ከተማ ነዋሪዎች መካከል 29 በመቶ ያህሉ የኮቪድ-19 አንቲቦዲ አዳብረው መገኘታቸው በጥናቱ ላይ ይፋ ተደርጓል።
ይህም ማለት 20 ሚሊየን ከሚሆነው የዴልሂ ከተማ ነዋሪ መካከል ስድስት ሚሊዮን ያህሉ በቫይረሱ ተይዘው አገግመዋል ማለት ነው።
የዴልሂ የጤና ሚኒስትር ሳታዬንድራ ሤይን ከተማቸው ለወረርሽኙ በማህበረሰብ ደረጃ መከላከያውን አዳብረዋል ለማለት ጊዜው ገና መሆኑን አስታውቀዋል።
በማህበረሰብ ደረጃ ተፈጥሯዊ መከላከያ ማዳበር (herd immunity) የሚባለው በቂ መጠን ያለው ሰው ቫይረሱን የመከላከል አቅም ሲያዳብር እና ስርጭቱን ባለበት ማቆም ሲቻል ነው።
" መጀመሪያ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ላይ ከነበረው 23 በመቶ አሁን 29 በመቶ ያህል ሰዎች አገግመው አንቲቦዲዎችን ማዳበራቸው መልካም ነው፤ ነገር ግን የማህበረሰብ የመከላከል አቅም ዳበረ የምንለው ከ40 እስከ 70 በመቶ ያህሉ አዳብረው ሲገኙ ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ተመሳሳይ ጥናት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ ባጠቃት ሙምባይና ፑኔ ከተሞች የተደረገ ሲሆን፣ ከተመረመሩት መካከል ከ40 በመቶ በላይ ሰዎች የቫይረሱን አንቲቦዲ አዳብረው ተገኝተዋል።
በፑኔ ምርመራው ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አንቲቦዲ ማዳበራቸውን የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት ያሳያል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት እንዲህ አይነት ጥናቶች ባለስልጣናትን የቫይረሱ ስርጭት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ግንዛቤ በመስጠት ረገድ ጥቅማቸው የትየለሌ ነው።
ጥናቱ እንዲሁ የመመርመሪያ ጣብያዎችን በተገቢው መልኩ ለማደራጀት እንዲሁም አንድ አካባቢን ብቻ ለይቶ የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣልና ቫይረሱን ለመቆጣጣር ያግዛል።
የሕንዷ ዴልሂ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጎዱ የሕንድ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን በሰኔ የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት የሆስፒታል አልጋዎች እጥረትም ተከስቶ ነበር።
አሁን የሆስፒታሎች ቁሳቁስ የተሟላ ሲሆን በየዕለቱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ቀንሷል።