ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ህንድ ከቻይና ልትፈጽመው የነበረውን ፈጣን መመርመሪያ መሳሪያዎችን ግዥ ሰረዘች
ህንድ ከቻይና ልትፈጽመው የነበረውን ወደ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጋ ፈጣን የመመርመሪያ መሳሪያ ግዢ ሰረዘች።
ምክንያቱ ደግሞ መሳሪያዎቹ በሥራ ላይ የጥራት ጉድለት ስለተገኘባቸው ነው።
ዴልሂም በተለያዩ ግዛቶች በአገልግሎት ላይ ሲውሉ የነበሩ የመመርመሪያ መሳሪያዎች ሥራ እንዲያቋረጡ አድርጋለች።
የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ደም ውስጥ የሚገኘውን በሽታ መከላከያ (አንቲ ቦዲስ) የመለየት አቅም ሊኖራቸው ይገባ ነበር።
ውጤቱንም ለማሳወቅ 30 ደቂቃ የሚወስድ ሲሆን ባለስልጣናት በተወሰነ አካባቢ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት በፍጥነት ለመረዳት ያስችላል ተብሎ ነበር።
ሆኖም ፈጣን መመርመሪያው የኮሮናቫይረስን መመርመር አልቻለም። በርካታ ተመራማሪዎችም መመርመሪያ መሳሪያዎቹን መጠቀም አሳስቧቸዋል።
ይሁን እንጂ ቻይና በህንድ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጋዋለች።
"ከቻይና የሚመጡ የህክምና ምርቶች ጥራት ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል። የተወሰኑ ግለሰቦች የቻይና ምርቶችን ለማጣጣል እና ሐሰተኛ ለማድረግ መሞከር እንዲሁም በጭፍን ጥላቻ መመልከት ፍትሃዊ ያልሆነና ኃላፊነት የጎደለው ነው" ሲሉ የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ጂ ሮንግ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ህንድ በቂ ምርመራ እያደረገች እንዳልሆነ ያሳሰባቸው በርካታ ግዛቶች ግን የህንድ የህክምና ጥናት ካውንስል (ICMR) የመመርመሪያ መሳሪያዎቹን ለመጠቀም እንዲፈቅድላቸው ግፊት ሲያደርጉ ነበር።
ተቋሙ በመጀመሪያ ላይ አመንትቶ የነበረ ቢሆንም ከሁለት የቻይና ካምፓኒዎች መሳሪያዎቹ እንዲገቡ መንገድ አመቻችቷል።
ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን ግዛቶቹ መሳሪያውን በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ ሰው ላይ መሞከራቸውንና ውጤቱም ከቫይረሱ ነጻ መሆኑን (ኔጋቲቭ) ማሳየቱን በመግለጽ፤ የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ ትክክለኛነት 5 በመቶ ብቻ ነው ሲሉ ቅሬታ ማቅረብ መጀመራቸው ተነግረወል።
ከዚያም መመርመሪያ መሳሪያዎቹ በተቋሙ በተደረገ ፍተሻ ጥራት የሌላቸው መሆናቸው ሊታወቅ ችሏል።
ሰኞ ዕለት የዴልሂ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወጣውን ገንዘብ በመጥቀስ መንግሥት ለመሳሪያዎቹ ከልክ በላይ ከፍሏል ካለ በኋላ ጉዳዩ የበለጠ ተወሳስቧል።
ይሁን እንጅ ባለሥልጣናት የመመርመሪያ መሳሪያዎቹን ለመግዛት ቅድመ ክፍያ ስላልፈጸሙና የማጓጓዙም ሥራ በመሰረዙ መንግሥት ምንም አይከስርም ሲሉ ለአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።