የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት አወጁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን አስታወቁ።
ትሪፖሊን መቀመጫው ያደረገው እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው መንግሥት የተኩስ አቁሙን በሚመለከት መግለጫ ያወጣ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመትም መጋቢት ወር ላይ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የትሪፖሊው መንግሥት ከጄነራል ካሊፍ ሃፍታር ከሚመራው ጦር ጋር በአገሪቱ ምስራቃዊ እና ደቡብ ክፍል ውጊያ ሲያደርግ ነበር።
በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት የሚደገፈው ጦር በ2011 ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊን ከሥልጣን ካወረደ ጊዜ ጀምሮ ሊቢያ በእርስ በእርስ ጦርነት እየተለበለበች ትገኛለች።
በነዳጅ ሃብት የበለፀገቸው ሊብያ ወደ አውሮጳ መሻገር ለሚፈልጉ አፍሪካውያን ዋነኛ መሸጋገሪያ ሆና እያገለገለች ነው።
በሊብያ የሚካሄደው ግጭት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መካከል መከፋፈል ፈጥሯል።
ባለፈው ወር ፈረንሳይ ቱርክ በሊቢያ ላይ የተጣለውን የመሳሪያ ማዕቀብ ትጥሳለች በሚል ቅሬታ አቅርባ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት በባህር ጥበቃ ላይ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ለጊዜው ራሷን አግልላለች።
በርግጥ አንካራ እጄ የለበትም ብትልም የቱርክ መርከብ የፈረንሳይ ጦር መርከብን በሜዲትራንያን ባህር ላይ ዒላማ በማድረግ ጥቃት መክፈቱ ከተሰማ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
በሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የተለያዩ አገራት እጃቸው እንዳለበት ይገለፃል።
ቱርክ፣ ጣልያን፣ እንዲሁም ኳታር የትሪፖሊውን መንግሥት ደግፈው፣ ሩሲያ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ደግሞ የጄነራል ሃፍታርን ጦር በመደገፍ ሊቢያን የጦርነት አውድማ ካደረጉ ቆይተዋል።
በርግጥ በፓሪስ የሚገኙ የፈረንሳይ ባለስልጣናት እውነትነቱን ባያረጋግጡም ፈረንሳይ ጄነራል ሃፍታርን ትረዳለች የሚል ጭምጭምታ አለ።
የተባበሩት መንግሥታት ወደ ሊቢያ የሚደረግ ማንኛውንም የጦር መሳርያ ዝውውር ያገደ ቢሆንም አሁንም አነስተኛ ውጤት ነው ማስገኘት የቻለው።
ቱርክ ከትሪፖሊው መንግሥት ጋር በ2019 ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማ ወታደሮቿን በሊብያ አስፍራለች።
በሰኔ ወር ደግሞ የትሪፖሊው መንግሥት በዋና ከተማዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር እንዳገኘ በማስታወቅ ቱርክን ስለ ድጋፏ አመስግኗል። ጄነራል ሃፍታር ከከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ጦራቸውን ማውጣታቸውም ተሰምቷል።
ከተባበሩት መንግሥት በግንቦት ወር ሾልኮ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በሊብያ ጄነራል ሃፍታርን በመደገፍ ተሰማርተዋል።














