የአውሮፓ አገራት ''ከአያቶላህ ጋር ወግነዋል'' ስትል አሜሪካ ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ እነ እንግሊዝን ‹‹እኔን ክዳችሁ ከአያቶላህ ጋር ወግናችኋል› ስትል ከሳለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ከአያቶላህ ጋር ወግናችኋል ሲሉ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አጋሮቻቸው የሆኑትን ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈንሳይን እና ጀርመንን አውግዘዋል።
በብዙ ፖለቲካዊ አሰላለፎች ከአሜሪካ መወገናቸው የሚጠበቀው እነ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን በማይክ ፖምፔዮ በክህደት የተወነጀሉ አገራት ናቸው። ውንጀላው አሜሪካ በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ እንዲራዘም መሻቷን ባለመደገፋቸው የመጣ ነው።
ማይክ ፖምፔዮ ኢራንን አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጧትና በጸጥታው ምክር ቤት ውድቅ የተደረገው ‹የማዕቀብ ይራዘም› ማመልከቻ ተመልሶ እንደሚተገበር አረጋግጠዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመንና ፈረንሳይ በበኩላቸው አሜሪካ በኢራን ላይ ማዕቀቡ ተመልሶ እንዲጣልባት የማድረግ ልዩ የሥልጣን ባለቤት አይደለችም፣ ሕጉም አይፈቅድላትም ብለዋል።
በሕግ ቋንቋ ‹ስናፕባክ› የሚባለው አሠራር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአንድ ጉዳይ ላይ ስምምነት የፈረሙ አባል አገራት አንዱ በሌላው ቅጣት የሚጥልበት አሰራር ነው።
አሁን አሜሪካ በዚህ የሕግ አግባብ ለመሄድ አትችልም የሚለው ነገር የመጣው ትራምፕ በራሳቸው ጊዜ ከኢራኑ የኑክሌር ስምምነት መውጣታቸውን ተከትሎ ነው። ስምምነቱ ውስጥ የሌለ አካል ደግሞ ስምምነቱ ውስጥ ያሉ አገራት የሚኖራቸውን የሕግ መብቱን ወዲያውኑ ያጣል።
ይህም በመሆኑ ነው አሜሪካ በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ይቀጥል ማለት አትችልም ያስባለው። ያም ሆኖ ግን አሜሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ይህ እንዲተገበር ይፋ ማመልከቻ አስገብታለች።
በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አሻንጉሊት ይሁን/አይሁን የሚፈተንበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ኢራን የተመጠኑ የመሣሪያ ግዢዎችንና ሽያጮችን ማከናወን እንድትችል ማዕቀብ እንዲነሳላት የተወሰነው ባለፈው ሳምንት ነበር።
ይህ ማዕቀብ እንዲነሳላት የሆነውም በ2015 ያደረገችውን የኑክሌር ስምምነት ተከትሎ ነው። በሌላ ቋንቋ በዚህ ጊዜ ማዕቀቡ ይነሳላታል የሚለው የዚህ የ2015ቱ የኑክሌር ስምምነት አካል ነበር። ማዕቀቡ ከዚህ ቀደም ተጥሎባት የነበረና በመጪው ጥቅምት ዘመኑ የሚያበቃ ነው።
የጸጥታው ምክር ቤት አባላትም በመጪው ጥቅምት ዘመኑ የሚቃጠለው ማዕቀብ ይነሳ ወይስ ይቀጥል በሚለው ጉዳይ ላይ ነበር ባለፈው ሳምንት ድምጽ የሰጡት። ‹‹ከአሜሪካ በስተቀር አንድም አገር በኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የማድረግ ወኔና ድፍረቱን አላገኘም።
እነዚያ አውሮጳዊያን አጋሮቻችን የምንላቸው እንኳ ከአያቶላህ መወገንን መርጠዋል›› ሲሉ ፖምፔዮ ውርጅብኝ አዝንበዋል፣ በምንጊዜም አጋሮቻቸው በነ እንግሊዝና ፈረንሳይ ላይ።
ፖምፒዮ ለጸጥታው ምክር ቤት ይፋ ደብዳቤ ያስገቡት ኢራን ለ2015ቱ የኒክሌር ስምምነት ተገዢ ስላልሆነች ማዕቀቡ እንዲነሳላት መወሰኑ አግባብ ስላልሆነ የተጣለባት ማዕቀብ ይራዘም ብሎ የሚጠይቅ ነው።
የዚህ ክስ አስገራሚ ገጽታ የሚሆነው ግን አሜሪካ ስምምነቱን ሳታከብር በ2018 ዓ.ም ከስምምነቱ ወጥታ ሳለ ስለ ስምምነቱ መከበር አለመከበር መናገር መቻሏ ነው።
አሜሪካ በበኩሏ ይህን ለማድረግ የሚከለክለኝ አንዳችም ነገር የለም ትላለች። ‹‹ከስምምነቱ መውጣቴ ይህን መብት አያሳጣኝም›› ይህን አሜሪካ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ያስገባችውን ማመልከቻ ሌሎች አገሮች በ30 ቀናት ውስጥ ውድቅ የማድረግ መብት አላቸው።
ችግሩ ግን አሜሪካ የፍጹማዊ ድምጽ (ቪቶ) ተጠቅማ ማመልከቻዋን ውድቅ ያደረጉባትን አገሮች ድምጻቸውን መልሳ ውድቅ ማድረግ መቻሏ ነው። ኢራን ዘለግ ላሉ ዓመታት የተጣለባት ማዕቀብ የተነሳላት ባለፈው ሳምንት ነበር።
አሜሪካ በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ እንዲቀጥል የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራትን ለማግባባት ባለፉት ሳምንታት ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ ገብታ የነበረ ቢሆንም አልተሳካላትም። ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ ውጭ አንድም አገር ድምጽ አልሰጣትም።
በድምጽ አሰጣጡ ድጋፍ ለማግኘት 9 ድምጽ ያስፈልጋት የነበረችው አሜሪካ በአንድ ድምጽ ወጥታለች። ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ዩናይትድ ኪንግደም ድምጸ ተአቅቦ ሲያደርጉ ሩሲያና ቻይና ‹ይነሳላት› በሚል ድምጽ ሰጥተዋል።
ኢራን ባለፈው ሳምንት በተሰጠው የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ተደስታለች። ‹‹አሜሪካ አሳፋሪ የዲፕሎማሲ ውርደት ነው ያጋጠማት› ብለዋል የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ።
ፖምፔዮ የጸጥታው ምክር ቤትን ውሳኔ ለመቀልበስ የሚጠይቀውን ማመልከቻ (ስናፕባክ) ይዘው የመጡትም በመጪው ጥቅምት የሚያበቃውን በኢራን ላይ የተጣለ ማዕቀብ ከወዲሁ እንዲነሳ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ነው፡፡
ማይክ ፖምፔዮ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ኢራን አሸባሪ አገር ናት፡፡ አሸባሪ አገር በፍጹም ኮንቬንሽናል የጦር መሣሪያ እንዲገዛና እንዲሸጥ ልንፈቅድ አይገባም፡፡ አሜሪካ አይኗ እያየ ይህ እንዲሆን አትፈቅድም፡፡ ኢራን ታንክ ስትቸበችብ አሜሪካ ቆማ አታይም›› ብለዋል፡፡

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካና አውሮጳዊያን ሆድና ጀርባ?
ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በተለይም ቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በአሜሪካና በአውሮጳ ዘንድ እንዲህ ያለ ንፋስ ገብቶ አያውቅም ይላሉ የአካባቢው ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ተንታኞች፡፡
አውሮጳዊያን ታሪካዊ አጋር አገራት ከፕሬዝዳንቶች ሁሉ ዶናልድ ትራምፕ ግራ የሚያጋቧቸው ይመስላል፡፡ ከኔቶ እወጣለሁ ብለው ሲያስቸግሯቸው ነበር፡፡ ከፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ድንገት ወጡባቸው፡፡
ከ2 ዓመት በፊት ደግሞ ብዙ ከተደከመበት የኢራን ኑክሌየር ስምምነት ወጡ፡፡ አሁን ለአውሮጳዊያኑ ተስፋቸው ጆ ባይደን ይመስላሉ፡፡ እንዴት እዚህ ደረጃ ተደረሰ የሚለውን በአጭሩ እንመልከት፡፡
በ2015 ዓ.ም የተፈረመውን ታሪካዊ የኑክሌር ስምምነት የፈረሙት አምስቱ ኃያላን እና ኢራን ናቸው፡፡ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ራሺያ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ጀርመን፡፡
ስምምነቱ በአጭሩ ኢራን የኑክሌር የጦር መሣሪያን እንዳታበለጽግ መከላከል ነው፡፡
ሆኖም ኢራን በዚህ ስምምነት መሰረት ለኃይል አቅርቦት የሚውል የኒክሌር ኃይልን ማበልጸግ ትችላለች፡፡ የዓለም አቀፍ መርማሪዎችም ኢራን ድብቅ የኒክሌር የጦር መሣሪያ እያበለጸገች እንዳልሆነ በየጊዜው አገሪቱ ውስጥ እየገባ እንዲከታተል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ይህን ስምምነት ባራክ ኦባማ ነበር የፈረሙት፡፡ ባራክ የባረኩት ነገር የማይጥማቸው ትራምፕ ግን ስምምነቱ ‹‹የጅሎች ስምምነት ነው›› በሚል ቀዳደው ጥለውታል፡፡
የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላም ሆኑ የፈንሳዩ ማክሮን ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ስምምነት እንዳይወጡ ተደጋጋሚ ማባበልና ውትወታ ቢያደርጉም ትራምፕ ጨክነዋል፡፡
የአሜሪካንን ከስምምነቱ መውጣት ተከትሎ ኢራን አውሮጳዊያኑ ምጣኔ ሐብታዊ ማካካሻ እስካላደረጉላት ድረስ በስምምነቱ ውስጥ ለመቆየት እንደምትቸገር በመግለጽ ወደ ኒክሌር ግንባታዬ መመለሴ ነው እያለች ስታስፈራራ ነበር፡፡
ኢራን ስምምነቱን እንዳታፈርስ አውሮጳዊያን የተለያዩ ማባበያዎቹን እያቀረቡ ነገሩ እዚህ ደርሷል፡፡ ኢራን አሁንም ቢሆን ከስምምነቱ ውስጥ የጣሰቻቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ዩራኒየም ማብሊያ ከሚፈቀድላት መጠን ማድረስና የባሊስቲክ ሚሳይል ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡
አምስቱ ኃያላን አሜሪካ ቀዳዳ የጣለችውን ስምምነት እንዳይፈርስ አሁንም ጥረት ላይ ናቸው፡፡
አሜሪካ ከኢራን ምንድነው የምትፈልገው?
አሜሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት ተከናንባ ብትወጣም የአሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ አምባሳደር ኬሊ ክራፍት ‹አሜሪካ የጸጥታው ምክር ቤቱን ውሳኔ ትቀለብሰዋለች›› ሲሉ አትጠራጠሩ ብለዋል፡፡
ረቡዕ ዶናልድ ትራምፕ ‹‹ኢራን ላይ በምድር ላይ አለ የሚባል ማዕቀብ ሁሉ ተመልሶ ይጫንባታል›› ሲሉ ዝተዋል፡፡ ኢራን በፍጹም የኒክሌር ባለቤት አትሆንም፤ የኔ አስተዳደር ይህ እንዲሆን አይፈቅድም በፍጹም ብለዋል ትራምፕ፡፡
አሜሪካ በኢራን ላይ ተጥሎ የቆየውና በመጪው ጥቅምት ዘመኑ ይገባደድ የነበረውን ማዕቀብ ተመልሶ እንዲቀጥል ብቻም ሳይሆን ከኒክሌየር ማብለያ ጋር ተያያዥ የሆኑ ማናቸውንም ነገሮች ኢራን ወደ አገሯ እንዳታስገባ ትፈልጋለች፡፡
በተጨማሪም በኢራን ኩባንያዎች፣ ባንኮች፣ ባለሀብቶችና ባለሥልጣናት ላይ ሊጣል የሚችሉ ማናቸውም ማዕቀቦች እንዲጣሉባት ወስናለች፡፡ ጃቫድ ዘሪፍ አሜሪካ እየሞከረች ያለችው ሕግን መተላለፍ ነው ብለዋል፡፡
በስምምነቱ ላይ አሁንም የቀጠሉት ሦስቱ የአውሮጳ መንግሥታትም አሜሪካ ይህን እንድታደርግ የሚፈቅድላት ሕግ የለም፤ ከስምምነቱ በ2018 በይፋ ወጥታለች፤ ስለዚህ በጋራ ስምምነቱ ያላትን መብት ያጣችው ያኔ ነው››ብለዋል፡፡
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ ‹‹የአሜሪካ ነገር ግራ አጋቢ ነው›› ብለዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀቡን ለመመለስ መብቱም ስልጣኑም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ተቃውሞው በዚህ መንገድ ይገለጽ እንጂ አገራቱ አሜሪካ ማድረግ ያሰበችውን ከማድረግ እንድትቆጠብ ለማድረግ መንገዱ አላቸው ወይ የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት የአሜረካ ሳሎን ቤት ነው የሚለው አባባል የሚፈተሸበት ወሳኝ ሰዓት የተደረሰ ይመስላል፡፡ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ፖለቲካ አዋቂዎች አውሮጳዊያን በዚህ ሰዓት ከአሜሪካ ጎን መቆም ያልሻቱት በመጪው ኅዳር ትራምፕ ከተሸነፉ ጆ ባይደን አሜሪካንን ወደዚህ የ2015ቱ የኒክሌየር ስምምነት መልሰው ሊያመጧት ይችላሉ በሚል ተስፋ ነው፡፡















