ኮሮናቫይረስ፡ ኒውዚላንድ 14 በከሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች አገኘች

በኦክላንድ ጭምብል ያጠለቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የኒውዚላንዷ ትልቋ ከተማ ኦክላንድ በድጋሚ የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለባት በኋላ አዲስ 14 በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተገለጸ።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ አራት አንድ የቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲሰማ መላው ኒውዚላንድ በድንጋጤ ተውጦ የነበረ ሲሆን የአሁኑ ደግሞ ነገሮችን አባብሷል።

ከውጭ አገራት በቫይረሱ ተይዘው ከሚመጡ ሰዎች ውጪ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ አገሪቱ ላለፉት ሶስት ወራት ምንም በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘችም ነበር።

ዛሬ ከተገኙት ተጨማሪ 14 ሰዎች መካከል 13ቱ ከዚሁ ቤተሰብ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን አንደኛው ግለሰብ ደግሞ ከሌላ አገር ወደ ኒውዚላንድ ገብቶ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ እንደሆነ ተገልጿል።

ከትላንት ረቡዕ ጀምሮ ደግሞ በኦክላንድ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።

'' ሁኔታው ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ማየት እንችላለን'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጃሲንዳ አርደርን። በሰጡት ጋዜታዊ መግለጫ ላይ አክለውም '' ጉዳዩ በተገቢው መንገድ ክትትል እየተደረገበት ነው፤ ፈጣንና ተገቢው እርምጃም ይወሰዳል'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ሁሉም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን ኃላፊዎች ያስታወቁ ሲሆን ከነሱ ጋር በማንኛውም መንገድ ንክኪ የነበራቸው ሰዎችም ክትትል እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል።

ኒውዚላንድ እስካሁን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በወሰደቻቸው ፈጣንና ውጤታማ እርምጃዎች ከመላው ዓለም ምስጋናና ሙገሳ ሲጎርፍላት ነበር።

ይህ ዜና ከተሰማ በኋላም በመላው አገሪቱ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ግዴታ የተደረገ ሲሆን ቫይረሱ በተገኘባት ኦክላንድ ደግሞ ጠንከር ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።

ከማክሰኞ በፊት በኒው ዚላንድ በአገር ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ሳታገኝ 102 ቀናት መቆየት የቻለች አገር ነበረች።

የአገሪቱ የጤና ኃላፊዎችና ሰራተኞች ቫይረሱ ከየት እንደተነሳ ለማወቅ በፍጥነት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተገልጿል። በኮቪድ-19 የተያዙት ሰዎች ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና የስራ ባልደረቦችም ተለይተው ምርመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

'' ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመለየት ያለእረፍት እየሰራን ነው። ምንጩ ከየት እንደሆነም ለማወቅ የምንችለውን ነገር በሙሉ እያደረግን ነው'' ብለዋል ብሄራዊ የጤና ኃላፊው አሽሊ ብሉምፊልድ።

ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በድጋሚ ሲያገረሽ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም። በርካታ የአውሮፓ አገራት ሁኔታዎች መሻሻል ሲያሳዩ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማንሳታቸውን ተከትሎ ቫይረሱ ሁለተኛ ዙር መስፋፋት ጀምሯል።

ቪየትናም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሳታገኝ 99 ቀናት ሳታገኝ ከቆየች በኋላ ዳ ናንግ በተባለችው ከተማ ስርጭቱ በድጋሚ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

በኒውዚላንድ ወረርሽኙ በድጋሚ መቀስቀሱ ምናልባት በሌሎች ከተሞችም የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል ሊያስገድድ እንደሚችል ተፈርቷል። አገሪቱ ደግሞ በሳምንታት ልዩነት ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነበረች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ምን አይነት ውሳኔዎች እንሚተላለፉ ነገ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

ኮሮና
Banner