የእሳት አደጋ፡ በቼክ ሪፐብሊክ ነበተነሳ እሳት 3 ህፃናትን ጨምሮ 11 ሰዎች ሞቱ

በቼክ ሪፐብሊክ፣ ቦሁሚን የተነሳው እሳት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በቼክ ሪፐብሊክ በአንድ ሕንፃ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ሦስት ህፃናትን ጨምሮ 11 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ።

ከሟቾቹ መካከል ስድስቱ በእሳቱ የሞቱ ሲሆን አምስቱ ከአደጋው ለማምለጥ ከ11ኛ ፎቅ ከዘለሉ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለት የእሳት አደጋ ሰራተኞችንና አንድ ፖሊስን ጨምሮ አስር ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

በሰሜን ምስራቅ ከተማ ቦሁሚን ቅዳሜ ዕለት በአንድ ሕንፃ ላይ ከነበረ ክፍል የተነሳው ይህ የእሳት አደጋ በአገሪቷ ታሪክ የተከሰተ አስከፊ አደጋ ነው ተብሏል።

ቦሁሚን ከተማ በቼክ ሪፐብሊክና በፖላንድ ሪፐብሊክ ድንበር ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን ከአገሪቷ ዋና መዲና ፕራግ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ከተማዋ የምትገኝበት የሞራቪያ ስሌሲያ ግዛት አስተዳዳሪ ኢቮ ቮንድራክ፤ "እሳቱ ሆነ ተብሎ እንዲነሳ የተደረገ ይመስላል" ብለዋል።

አንድ ግለሰብ እሳቱን ያስነሳው እርሱ እንደሆነ ካመነ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ጃን ሃማሴክም የተከሰተው አደጋ አሳዛኝ እንደሆነ በመግለፅ በጎረቤቶች መካከል ለረዥም ጊዜ በዘለቀ ግጭት ሳቢያ የተፈጠረ ይመስላል ሲሉ ለቼክ ራዲዮ ተናግረዋል።

ፖሊስ በተነሱት ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አረጋግጦ፤ጉዳዩንም እየመረመረ መሆኑን ገልጿል።

የግዛቷ የእሳት አደጋ መከላከያ ቡድን ኃላፊ ቭላድሚር ቭልሴክ በበኩላቸው ያጋጠመው አይነት የእሳት አደጋ አንድ ክፍልን ብቻ ካወደመ በኋላ የሚገታ መሆኑን ገልፀው፤ ይህኛው ግን ባልተለመደ መልኩ በፍጥነት እንደተዛመተና ሁሉም ክፍሎች እንደተቃጠሉ ለአገሪቷ ቴሌቪዥን አስረድተዋል።