ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን በስለላ የተጠረጠረችው መምህርት ወደ 'አስከፊ' እስር ቤት መዛወሯ ተገለፀ
በኢራን በስለላ ወንጀል የ10 ዓመታትን በእስር እንድታሳልፍ የተፈረደባት እንግሊዛዊ አውስትራሊያዊቷ መምህርት ከነበረችበት እስር ቤት በአስከፊነቱ በሚታወቀው ና በበርሃ ላይ ወደሚገኝ እስር ቤት መዛወሯን የኢራን የሰብዓዊ መበት ተሟጋቾች ገለፁ።
መምህሯ በስለላ ወንጀል ትከሰስ እንጂ እርሷ ግን የቀረቡባትን ሁሉንም ክሶች ተቃውማለች።
በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረችው ክይሌ ሞር ጊልበርት ከጎርጎሮሳዊያኑ መስከረም 2018 አንስቶ በእስር ላይ ትገኛለች።
ሁለቱን ዓመታቱን የእስር ጊዜም በኢራን ዋና መዲና ቴህራን በሚገኝ እስር ቤት በአንድ ትንሽ ክፍል መሬት ላይ እየተኛች ማሳለፏን ጓደኛዋ ተናግራለች።
ግለሰቧ በእነዚህ ጊዜያት ከቤተሰብ ጋር ግንኙነት ሳይኖራት እና የርሃብ አድማ ስታደርግ ቆይታለች። እርሷ እንደምትለው ማስታወሻ በመላክና ግድግዳ ላይ በመፃፍ አዲስ እስረኞችን ለማፅናናት በመሞከሯም ድብደባ ደርሶባታል።
በአሁኑ ወቅት በበርሃ ላይ ወደሚገኘው አስከፊው ቃርቻክ እስር ቤት መዛወሯ ተሰምቷል።
እስር ቤቱ የኢራን የፖለቲከኛ እስረኞችን ለመቅጣት ይጠቀሙበት የነበረ እንደሆነ የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዘጋቢ ካሮሊን ሃውሊይ ዘግባለች። የቀድሞ ታሳሪዎች በእስር ቤቱ ያለውን ሁኔታም "አስቀያሚ እና አስፈሪ" ሲሉ ይገልፁታል።
የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ መምህርቷ ሞር፤ መደወል የቻለችው አንድ ጊዜ ሲሆን ለኢራናዊያን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በመጥፎ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ፣ ድብታ ውስጥ እንደገባችና ምግብም መመገብ እንዳልቻለች ተናግራለች።
ከቴህራን እስር ቤት በድብቅ በወጣው ደብዳቤዋ ላይም ሰላይ እንዳልነበረች፤ ነገር ግን "ከኢራን የቀረበላትን ሰላይ ሁኝ ጥያቄ" አልቀበልም ማለቷን አስታውሳለች። የአዕምሮ ጤናዋም ስጋት እንደሆነባት ገልፃለች ክሌይ ሞር ።
የካምብሪጅ ምሩቋ በአውስትራሊያ ፓስፖርት ወደ ቴህራን ያቀናችውና አንድ ስብሰባ አጠናቃ ለመመለስ ስትሞክር በቴህራን አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር የዋለችው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር።