በግድቡ የተጠራቀመው ውሃ በቀጣይ ዓመት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ያስችላል ተባለ

የሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a

ታትሟል

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ድግብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ይፋ ከሆነ በኋላ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ በቀጣይ ዓመት በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ገለጹ።

ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፤ ኢ/ር ) እንዳሉት ትናንት ምሽት ታላቁ የህዳሴ ግድብ “የሚያስፈልገውን 4.9 ቢ.ኪዩቢክ ሜትር በመያዝ ከግድቡ አናት ላይ ፈሷል ይህም የተሳካው ወደታችኛው ተፋሰስ የሚሄደው ውሃ ሳይቋረጥ ነው” ብለዋል።

በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ይህ ውጤት ዋነኛ ምዕራፍ ነው። ይህ በግድቡ የተያዘው ውሃ በመጪው ዓመት በሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ያስችለናል፤ ግንባታችንም ይቀጥላል” ብለዋል ሚንስትሩ።

ሚኒስትር ስለሺ ከመልዕክታቸው በተጨማሪ ግድቡ ሞልቶ ውሃው በግድቡ አናት ላይ ሲፈስ የሚያሳይ ምስል በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል። ይህም እንደተባለው ግድቡ ውሃ መያዙን የሚያመላክት ምስል በትዊተር ገጻቸው አውጥተዋል።

ሚኒስትሩ የእንኳን ደስ ያለን መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት የትዊተር ጽሑፍ ላይ ግድቡ ከመሞላቱ በፊት እና ከሞላ በኋላ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ለጥፈዋል።

ስለሺ (ዶ/ር፤ ኢ/ር) ያጋሩት ግድቡ ውሃ ከመያዙ በፊት የነበረው ገጽታ ከዚህ በታች ያለው ነው።

ገድቡ ውሃ መያዝ ከመጀመሩ በፊት

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a

ገድቡ ውሃ መያዝ ከጀመረ በኋላ ደግሞ ይህን ይመስላል።

ገድቡ ውሃ መያዝ ከጀመረ በኋላ ደግሞ ይህን ይመስላል።

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a

ትናንት ምሽት የተደረገው የመሪዎች ውይይት "የሰከነና ጥሩ ነበር” ያሉት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትሩ፤ “ስምምነት ባልተደረሰባቸው የቴክኒክና የሕግ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ በቀጣይ ጉዳዮች አካሄድ ስምምነት ተደርጓል” ብለዋል።

በዚህም መሰረት፤ “የሁሉም ደረጃ ውሃ ሙሊት ጉዳይ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ስምምነት እንዲደረስ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የሆነ ስምምነት፤ የወደፊት የውሃ አጠቃቀምን ጨምሮ በወደፊት ድርድሮች እንዲቋጩ መሪዎቹ ወስነዋል” ብለዋል።