የትምህርት ቤት የቤት ስራ ያልሰራችው ጥቁር አሜሪካዊቷ ተማሪ መታሰሯ ተቃውሞ ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንዲት የአስራ አምስት አመት ታዳጊ የቤት ስራዋን ባለማጠናቀቋ የሚቺጋን ዳኛ እስር ማዘዛቸውን ተከትሎ ተቃውሞ ተነስቷል።
ታዳጊዋ ከዚህ ቀደም በሰራቸው ወንጀል በማስጠንቀቂያ ታልፋ የነበረ ሲሆን አሁን በበይነመረብ የሚሰጠውን የቤት ስራ ባለመስራቷ ያንን በምክር ታልፋ የነበረውን ሁኔታ ጥሰሻል በሚልም ነው እስር የተወሰነባት።
ጥቁር አሜሪካዊቷ ታዳጊ ግሬስ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮም በእስር ላይ ነች ተብሏል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቷ እንዲሁም ከፍርድ ቤቱ ደጃፍ ተሰባስበውም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት ጉዳይዋን እንደገና እንደሚያየውም አስታውቋል።
ፕሮ ፐብሊካ በዚህ ሳምንት ባወጣው ፅሁፍም የታዳጊዋን እናት ቃለ መጠይቅ በማድረግ ግሬስ ያለባትንም ህመም አስፍሯል።
ሚያዝያ ወር ላይ እቃ ሰርቀሻል እንዲሁም ጥቃት ፈፅመሻል በሚል ተወንጅላ በዙም ፍርድ ቤት ቀርባ የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱም በማስጠንቀቂያ አልፏታል። ባህርይዋ ክትትል እንዲደረግበት በሚልም ፍርድ ቤቱ ሲወስን የትምህርት ቤት ጥናቶቿንና የቤት ስራዎቿን ማከናወን የአመክሮው አንድ አካልም ነው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሮ ፐብሊካ እንደዘገበው ግሬስ በማስጠንቀቂያ የታለፈችበት ቀንም ትምህርት ቤት በበይነ መረብ እንዲሆን የተወሰነበት ጋር ከመገጣጠሙ አንፃር፤ በቅርበት ድጋፍ የሚሰጡ መምህራን ባለማግኘቷም ፈታኝ ሆኖባት እንደነበር አስፍሯል።
ግንቦት ወር አጋማሽ ላይም የኦክላንድ ግዛት የቤተሰብ ፍርድ ቤት ክፍል ይህንን አመክሮ ጥሳ እንደሆነ ያየ ሲሆን ዳኛ ሜሪ ኤለን ብሬናን የትምህርት ቤት የቤት ስራ አለመስራቷ በማስጠንቀቂያ የታለፈችበትን ጥሳለች "ለማህበረሰቡም ጠንቅ ናት" በማለት እንድታተሰር ወስነዋል።
በግሮቭስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ግሬስ እንድትለቀቅ ፊርማቸውን አኑረዋል።
"በርካታ ተማሪዎች በዚህ መንፈቀ አመት ወደኋላ ቀርተዋል። የቤት ስራ ለመስራት ብዙዎች ፍላጎትም የላቸውም፤ እየሰሩም አይደለም። መምህራንም በበይነ መረብ ብዙ እያስተማሩ አይደለም።" በማለት የ18 አመቷ ተማሪ ፕሩደንስ ካንተር ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግራለች።
የማህበራዊ ጥናት መምህር ጆፍ ዊከርሻም ለሮይተርስ እንደተናገሩት "ጉዳይዋን ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎችም ሆኑ ዳኛዋ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት የትምህርት አሰጣጡን፣ የቤት ስራም ሆነ ፈተና እንዴት እንደተቀየረ አልገባቸውም። ግሬስ ላይ የወሰኑት ኢ-ፍትሃዊ ነው" ብለዋል።
ግሬስ ነፃ ትውጣ ከሚሉ መፈክሮችም ጋር ብላክ ላይቭስ ማተርም የሚሉ መፈክሮችም ጎን ለጎን ሰልፈኞች ይዘው ነበር።
"ግሬስ ነጭ ተማሪ ብትሆን በቁጥጥር ስር አትውልም፤ ማረሚያ ቤትም አትገባም" በማለት እናቷ ሼሪ ክራውሊ ለአካባቢው ሚዲያ ተናግረዋል።
የግሬስ ጠበቆች በአስቸኳይ ሁኔታዋ እንዲታይ መጠየቃቸውን ተከትሎ የሚቺጋን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳይዋን እንደገና እንደሚያየው አሳውቋል።












