አሜሪካ ደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሊነሳ ይችላል አለች

ለደቡብ ሱዳን ጸጥታ መደፍረስ ታጣቂ ኃይሎች እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለደቡብ ሱዳን ጸጥታ መደፍረስ ታጣቂ ኃይሎች እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ
ታትሟል

አሜሪካ ደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሊነሳ ይችላል አለች።

አሜሪካ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች የሚሟሉ ከሆነ ደቡብ ሱዳን ላይ ተጥሎ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሊነሳ እንደሚችል አስታወቀች።

ተሳናባቹ በደቡብ ሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ቶማስ ሁሼክ አሜሪካ ያሰቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች የሚፈጸሙ ከሆነ ደቡብ ሱዳን ላይ ተጥሎ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንደሚነሳ ጠቁመዋል።

ከተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በደቡብ ሱዳን የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ "የሙስና እና ግጭት መጠን መቀነስ ይኖርበታል" የሚለው ይገኝበታል።

ባለፈው ግንቦት ወር የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደቡብ ሱዳን ላይ ተጥሎ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ለአንድ ዓመት እንዲራዘመ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥትም በተመረጡ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባለስልጣናት ላይ ማዕቀቦችን ጥሎ ይገኛል። ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል የቀድሞ ምክትል ፕሬዝደንት ታባን ዴንግ ጋይ ይገኙበታል።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ንብረቶቻቸውን እንዳያንቀሳቅሱ በአሜሪካ እግድ ተጥሎባቸዋል።

ተሰናባቹ አምባሳደር ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ በደቡብ ሱዳን እና ባለስልጣናት ላይ ተጥሎ የሚገኘው ዘረፈ ብዙ ማዕቀብ የሚሻሻልበት አማራጭ እንደሚኖር ተናግረዋል።

"ተጥለው የሚገኙ ማዕቀቦች ሊነሱ ስለሚችሉበት አማራጮች ለመንግሥት እቅድ አቅርበናል" ያሉት ተሰናባቹ አምባሳደር ቶማስ ሁሼክ፤ በአገሪቱ የፋይናንስ ግልጽነት እንዲኖርም ከመንግሥት ጋር እየመከርን ነው ብለዋል።