ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ የቀድሞው ቅኝ ገዥ ሰሲል ሮድስ ሃውልት ጭንቅላት ተቆረጠ
በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን የእንግሊዛዊውን ቅኝ ገዥ ሰሲል ሮድስ ሃውልት ጭንቅላት ተቆረጠ።
ከነሃስ የተሰራው ይህ ሃውልት በባለፈው ሳምንት እሁድ ጭንቅላቱ መቆረጡንም የደቡብ አፍሪካ ፓርክ አስታውቋል።
በነጭ ፖሊስ ተደፍቆ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ የበርካታ ባርያ ፈንጋዮች፣ ጨፍጫፊዎችና ዘረኞች ሃውልት ተገርስሷል። ከዚህም በተጨማሪ በመላው አለምም ከፍተኛ ተቃውሞንም አቀጣጥሏል።
ነጭ ፅንፈኛውና ዘረኛው ሮድስ የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የመራ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካንም እንደ ሰም አቅልጦ በመግዛት ማዕድኗን በዝብዟል፤ ሃብትንም አፍርቷል።
በርካቶችም የኢምፔሪያሊዝምና የዘረኝነትም ሃውልት ስለሆነ ሃውልቱ ይገርሰስ በሚልም ዘመቻ ተደርጓል።
የሮድስ ማስታወሻ ሃውልት በኬፕታውን የቆመው በጎርጎሳውያኑ 1912 ነበር። የደቡብ አፍሪካ ፓርክም የሃውልቱን ጉዳት በተመለከተ ለፖሊስ ማሳወቁን ገልጿል።
ሃውልቱ መጀመሪያ ላይ ጉዳት የደረሰበት በጎርጎሳውያኑ 2001 ሲሆን ቀይ ቀለምም ተደፍቶበት ነበር።
ከሶስት አመት በፊትም አፍንጫው ተቆርጦ እንደገና ታድሷል።
በኬፕታውን ዩኒቨርስቲ የሚገኘው የቀድሞው ቅኝ ገዥ ሃውልት በጎርጎሮሳውያኑ 2015 "ጨፍጫፊዎችና ቅኝ ገዥዎች መውደቅ" አለባቸው የሚለውን ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲገረሰስ ተደርጓል።
በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ታሪክ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ጨካኙ ሮድስ በስሙም የአሁኗን ዚምባብዌ የቀድሞዋን ሮዴዥያ በሚልም ገዝቷል።
እንግሊዛውያን ከሁሉም ዘሮች የተመረጡ ናቸው የሚልም ጭፍንና ጠባብ ነበርም ይባላል። ደቡብ አፍሪካና ዚምባብዌ በነጭ አናሳዎችም ለዘመናት ተገዝተዋል፤ ተጨፍጭፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ሃውልትም ይገርሰስ ጥያቄዎች በርክተዋል።