ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት ወቅት የወሰደቻቸውን የአልጀሪያ የነፃነት ታጋዮች የራስ ቅል አፅም ልትመልስ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት ወቅት እንደ ሽልማት የወሰደቻቸውን 24 የሚሆኑ የአልጀሪያ ነፃነት ታጋዮችን የራስ ቅል አፅም ልትመልስ ነው።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይን ቅኝ ግዛት ሲታገሉ የተሰዉ ናቸው ተብሏል።
የአልጀሪያው ፕሬዚዳንት አብደልማድጂድ ቴቡን ሃገሪቷ ውስጥ በትናንትናው ዕለት በነበረ የጦር ክብረ በዓል ላይ ነው ውሳኔውን ያሳወቁት።
የነፃነት ታጋዮቹ የራስ ቅል አፅምም በመዲናዋ ፓሪስ በሚገኝ ሙዚየም ውስጥ ሲጎበኝም ነበር።
አልጀሪያ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችው በጎርጎሳውያኑ 1962 ሲሆን ለሰባት አመታትም ያህል እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግም ለክፍለ ዘመናት የቆየው ቅኝ ግዛት መቋጫ ሆኗል።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሰሜን አፍሪካን ቅኝ ግዛት "በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ጥፋት" ብለውታል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ምንም እንኳን ታሪካዊ ጥፋቶችና አሳዛኝ ነገሮች ቢፈፀሙም የሃገራቸውንና የአልጀሪያ ግንኙነት መሻሻል እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
የአልጀሪያ ፕሬዚዳንት ቴቡን እንደገለፁት የአልጀሪያ ጦር አውሮፕላን ወደ ፈረንሳይ እንደሚገባና የቀሩትን 24 የነፃነት ታጋዮች አፅምም እንደሚያመጣ ነው።
የአንዳንዶቹም አፅምም የእምቢተኝነት ተምሳሌት የሆኑት አመራር ናቸው ተብሏል።
ከነዚህም መካከል በጎርጎሳውያኑ 1849 ተይዞ በጥይት ገድለው አንገቱን የቀሉት ሼክ ቡዚያን ይገኝበታል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም እነዚህ የነፃነት ታጋዮች "አስከሬናቸው መሬት ሳያርፍ የተፈጥሮና ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ ለ170 አመታት ያህል ቆይቷል" ብለዋል።
የአርባዎቹ የነፃነት ታጋዮች የራስ ቅልም እንደ ሽልማት ተወስዶ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በሚገኘው የብሔራዊ ሙዚየምም ሲጎበኝ ነበር።
የአልጀሪያና የፈረንሳይ ታሪክ ምሁራንና ልሂቃን እነዚህ የራስ ቅል አፅሞች እንዲመለሱ ጥሪ ለአመታትም ሲያካሂዱ ነበር።












