ቼክ ሪፐብሊክ ኮሮናቫይረስን 'ደህና ሁን' ስትል ደግሳ ተሰናበተች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከምድራችን የመጥፊያ ቀን እጅጉን የራቀ መሆኑን ያሳወቀው በዚህ ሳምንት ነበር። ነገር ግን ቼክ ሪፐብሊክ ደግሳ ኮሮናቫይረስን "ደህና ሁን" ስትል ተሰናብታዋለች።
ማክሰኞ እለት በፕራግ በሚገኘው ቻርልስ ድልድይ ላይ 500 ሜትር በሚረዝም ጠረጴዛ ዙሪያ የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤታቸው ይዘውት የመጡትን መጠጥና ምግብ በጋራ ተቋድሰዋል።
እንግዶች አጠገባቸው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ምግብ የተጋሩ ሲሆን ማህበራዊም ሆነ አካላዊ ርቀት አይስተዋልም ነበር ተብሏል። ይህ ደግሞ በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ በቆዩ ከተሞች ሁሉ ያልተስተዋለ ነው ተብሏል።
10 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ቼክ ሪፐብሊክ የኮቪድ-19 እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 12 ሺህ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 350 ሰዎች ሞተዋል።
ይህንን ፈንጠዝያ ያዘጋጁት አካላት እንደተናገሩት በዚህች ዝነኛ የቱሪስት መስህብ ከተማ ጎብኚ በመጥፋቱ ሊካሄድ ችሏል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በፈንጠዝያው ላይ የተነሱ ምስሎች እንደሚያሳዩት ሰዎች ተጠጋግተው በመቀመጥ ሲመገቡ፣ ሲጠጡና ትርዒቶችን ሲመለከቱ ይታያል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images


የፎቶው ባለመብት, EPA
ኦንድሬጅ ኮብዛ ይህንን ፈንጠዝያ ካዘጋጁት መካከል አንዱ ሲሆን በከተማዋ ውስጥም ካፍቴሪያ አለው። ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ስለበዓሉ ሲናገር " የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማብቃትን ሰዎች አደባባይ ወጥተው በመገናኘት እንዲሁም ከጎረቤታቸው ጋር ምግብ መቋደስ እንደማይፈሩ በማሳየት እንዲያከብሩት እንፈልጋለን" ብሏል።
በዚህ ድግስ ላይ ለመገኘት አስቀድሞ ቦታ ማስያዝ ያስፈልግ የነበረ ሲሆን ያሉት ስፍራዎች ሁሉ የሞሉት ፈንጠዝያው ከመጀመሩ አስቀድሞ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዝግጅቱ ላይ ከታደሙት መካከል አንዷ የሆነችው ጋሊና ኮህምቼንኮ ስለ ድግሱ የሰማችው በፌስ ቡክ መሆኑን ገልፃ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።
"ከስራ አምሽቼ ነው የወጣሁት፤ እናም ምግብ አዘጋጅቶ ለመምጣት አልቻልኩም፤ ነገር ግን በቤቴ ያገኘሁትን ወይንና ጣፋጮች ይዤያለሁ" ስትል ተናግራለች።
ቼክ ሪፐብሊክ የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለችው ወረርሽኙ እንደተከሰተ ሲሆን በዚህም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ችላ እንደነበር ይነገራል።
ባለፈው ሳምንት መንግሥት እስከ አንድ ሺህ ሰዎች ድረስ በአደባባይ መሰብሰብ ይችላሉ ሲል ፈቅዷል። ዋና፣ ሙዚየሞች፣ መካነ አራዊቶች እንዲሁም ቤተ መንግሥቶች ክፍት ሲሆኑ የጎብኚዎች ቁጥርም አልተገደበባቸውም።
ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶችም እንግዶቻቸውን በቤት ውስጥ ማስተናገድ እንደሚችሉ ከተፈቀደ አንድ ወር ሆኖታል።













