ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ የተለያዩ ግዛቶች የወረደ መብረቅ ከ100 በላይ ሰዎችን ገደለ
በሰሜናዊ ሕንድ በሚገኙ ሁለት ግዛቶች ባለፈው ሳምንት ውስጥ ባጋጠሙ የመብረቅ አደጋዎች ምክንያት ከ100 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ቢሐር በምትባለው ግዛት ውስጥ የሚገኘው የአደጋ ተቆጣጠሪ ቡድን እንዳለው በግዛቲቱ 83 ሰዎች በመብረቅ የሞቱ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል።
ከዚህ ግዛት በተጨማሪም ጎረቤት በሆነችው ኡታር ፕራዴሽ ውስጥ ቢያንስ 20 ሰዎች በመብረቅ ተመትተው ለሞት መዳረጋቸው ተነግሯል።
ሕንድ ውስጥ ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት የመብረቅ አደጋ መከሰት የተለመደ ነው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ በአገሪቱ የሚጥለው ከባድ ዝናብና መብረቅ በበርካታ ቦታዎች ላይ በንብረትና በዛፎች ላይ ጉዳትን አስከትሏል።
የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ተጨማሪ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆማቸው ባለስልጣናት ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ አስጠንቅቀዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ለአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የቢሐር አደጋ መከላከል ባለስለጣን ለአኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በግዛቲቱ በሰዎች ላይ የደረሰው የመብረቅ ጉዳት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተመዘገቡት ሁሉ ከፍተኛው ነው። በአደጋው ከሞቱት ሰዎች ከግማሽ የሚልቁት በግዛቲቱ ሰሜናዊና ምሥራቃዊ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።
በኡታር ፕራዴሽ ግዛት ደግሞ አብዛኛው ሰዎች በመብረቅ የሞቱት ወደ ኔፓል ድንበር በሚጠጋው አካባቢ እና ቅዱስ ከተማ በምትባለው ፕራያግራጃ ውስጥ መሆኑን ባለስልጣናት አመልክተዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ከ2,300 በላይ ሰዎች ሕንድ ውስጥ በመብረቅ የሞቱ ሲሆን፤ ከአምስት ዓመት ወዲህ በየዓመቱ ቢያንስ 2,000 ሰዎች በአገሪቱ በመብረቅ እንደሚሞቱ ብሔራዊው የወንጀል ድርጊቶችን የሚመዘግበው ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በሕንድ እንዲህ ያለው በመብረቅ የሚከሰት ከፍተኛ የሞት ቁጥር እንዲመዘገብ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል ከሌሎች አገራት በተለያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዝናብ ከቤት ውጪ ሥራ ላይ ስለሚሆኑ ነው ተብሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት በደቡባዊ ሕንድ የምትገኘው አንድራ ፕራዴሽ ግዛት በ13 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 36,749 የመብረቅ አደጋዎች መከሰታቸው ተመዝግቧል።