የሶሪያው ባሻር አል አሳድ አጎት በፓሪስ ተፈረደባቸው

ሪፋት አል አሳድ
የምስሉ መግለጫ, ሪፋት አል አሳድ
ታትሟል

የሶሪያው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ አጎት በፈረንሳይ ፓሪስ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ አራት ዓመት ተፈርዶባቸው ዘብጥያ ወርደዋል።

የተከሰሱበት ወንጀል በሕገወጥ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ አስገብቶ በማጭበርበር ወንጀል ነው።

ሪፋት አል አሳድ እጃቸው በደም ጨቅይቷል የሚባሉት የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ አጎት ናቸው።

ከሶሪያ መንግሥት የሚሾልክላቸውን የሕዝብ ገንዘብ ወድ ቤቶችናና ቢሮዎችን በመግዛት ያባክናሉ ተብለው የተከሰሱት ሪፋት አል አሳድ 80 ሚሊዮን ፓውንድ በዚህ መንገድ ወጪ አድርገው የተቀናጣ ኑሮ መሥርተው በፓሪስና በስፔን ይኖሩ ነበር።

ሪፋት አል አሳድ ከዚህ ቀደም የሶሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ። አሁን የ82 ዓመት አዛውንት ናቸው።

በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሰረት የፓሪስና የሎንዶን ንብረቶቻቸው በሙሉ እንዲታገዱ ተወስኗል።

ሪፋት በታኅሣስ ወር የጭንቅላት ውስጥ መድማት አደጋ አጋጥሟቸው ስለነበር ሆስፒታል ነው የሰነበቱት።

የፍርድ ውሳኔው ዕለትም ፍርድ ቤት አልተገኙም። በጤናቸውና ዕድሜያቸው ምክንያት የተፈረደባቸውን ፍርድ ተፈጻሚ ላይሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለ።

የሪፋት አል አሳድ ሎንዶን የሚገኘው ንብረት ብቻ 26 ሚሊዮን ፓውንድ ይገመታል።

ሪፋት አል አሳድ ማን ነበሩ?

እኚህ ሰው በአንድ ወቅት በሶሪያ ሁለተኛው እጅግ የሚፈሩ ባለሥልጣን ነበሩ።

ወንድማቸው ሀፊዝ በሥልጣን ላይ ሳሉ ሪፋት የሰራዊቱ አዛዥ ነበር። ወንድማቸው ሃፊዝ ከ1971 ጀምሮ እስከሚሞቱበት 2000 እንደ አውሮጳዊያኑ ሶሪያን በአንቀጥቅጠህ ግዛ ሥነ አስተዳደር መርቷል።

ሪፋት አልአሳድ በቅጽል ስማቸው የሀማው አራጅ በሚል በሶሪያዊያ ዘንድ ይታወቃሉ። ይህን ስም ያገኙትም በ1982 በሶሪያ ሀማ ከተማ ተቀስቅሶ የነበረውን ተቃውሞ ዘግናኝ በሆነ ጭካኔ ጭጭ በማድረጋቸው ነው።

ሰዎችን ቤታቸው ውስጥ ሳሉ እሳት እየለኮሱ በማንደድ እና ያለምንም ርህራሄ ሕጻናትን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኘውን ሕዝብ መረሸንን ያካትት ነበር። ሪፋት አል አሳድ ይህንን የሀማን ኦፕሬሽን መርተዋል።

በዚህ የሪፋት አልአሳድ እርምጃ ከ10 እስከ 20ሺህ ሰዎች በቀናት ውስጥ መገደላቸው ይገመታል። ይህን አሀዝ አንዳንዶች ወደ 40ሺህ ያደርሱታል።

ሪፋት አልአሳድ በመጨረሻም በ1984 በወንድማቸው ሃፊዝ አልአሳድ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ሞክረው ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ከዚያ ወዲህ በፈረንሳይና በስፔን በስደት የተቀናጣ ሕይወት እየመሩ ይገኛል።

ወንድማቸው ሃፊዝ አልአሳድ እንደ አውሮጳዊያኑ በ2000 ላይ ሲሞቱ ሪፋት አልአሳድ ህጋዊው ወራሽ እኔ ነኝ ቢሉም የዛሬው ባሸር አል አሳድ ሥልጣኑን አጋጣሚ በሚመስል መልኩ ወስደውታል። ባሻር አል አሳድ የአይን ሐኪም (ኦፕቲሞሎጂ) ትምህርት ላይ ነበሩ። ለሥልጣን የታጩም ሰው አልነበሩም።

በ2011 ሶሪያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ስትገባ ሪፋት የወንድሙ ልጅ የሆነውን ባሻር አል አሳድን ሥልጣን እንዲለቅ ጠይቆ ነበር።

ለምን በፈረንሳይ ተከሰሱ?

ሪፋት አል አሳድ በ2014 ነው ክስ የተከፈተባቸው።

ሸርፓ የተባለ አንድ የምጣኔ ሀብትና ተያያዥ ወንጀሎች ላይ የሚሰራ ድርጅት የዚህ ሰው ሀብትና ንብረት በህጋዊ መንገድ ከሚያገኘው ገቢ ጋር የማይመጣጠን ስለሆነ ይመርመርልኝ የሚል መዝገብ ከፈተ።

ከአምስት ዓመት በኋላ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ሰውየው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ሲል ወሰነ። ከክሶቹም መሀል በሥልጣን ዘመኑ ያደረሰው ግፍ፣ ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ ማድረግና የሶሪያ ሕዝብ ንብረት የሆነን ገንዘብ ማባከን የሚል ነበሩ።

የፍርድ ሂደቱ መታየት የጀመረው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ሲሆን ሪፋት አል አሳድ ክሱን ያስተባበለው አሁን ያለኝ ሀብት ዘርፌው ሳይሆን የሳኡዲ ንጉሣዊያን ቤተሰብ በስጦታ የሰጠኝ ነው በሚል ነው።

ሪፋት በፈረንሳይ ቅንጡ ቤቶችና በሊዮን ከተማ ደግሞ ልዩ ልዩ ዘመናዊ ቢሮዎች በስሙ ይገኛሉ።

አሳድና ቤተሰቡ በስፔን ብቻ 587 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ንብረት አላቸው።

በ2017 የስፔን መንግሥት እነዚህ የአሳድ ቤተሰብ ንብረቶች እንዲታገዱ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።