"ቤት የመቀመጥ ግዳጅ ተግባራዊ ባይሆን ኖሮ በአውሮፓ ብቻ 3 ሚሊዮን ሰዎች ይሞቱ ነበር" ጥናት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቤት መቀመጥ ግዳጅ ተገባራዊ በመደረጉ በአውሮፓ ብቻ የ3 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ሊተርፍ መቻሉን አንድ ጥናት አመለከተ።
ለንደን በሚገኘው በኢምፔሪያል ኮሌጅ አንድ ቡድን ያደረገው ሰፊ ጥናት እንዳስገነዘበው ከሆነ አውሮፓ ያን እርምጃ ባትወስድ ኖሮ ጎዳናዎቿ በሬሳ በተሞሉ ነበር።
አንድ ሌላ ጥናትም በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የእንቅስቃሴ እቀባ መደረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቶ ሺህ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል ሲል ደምድሟል።
ኮሌጁ ይፋ ያደረገው ይህ የምርምር ወረቀት የ11 አገራትን የእንቅስቃሴ እቀባ ናሙና በመውሰድ የተደረገ መጠነ ሰፊ ጥናት ሲሆን ኦስትሪያ፣ ቤልጅየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም እስከ ግንቦት መጀመርያ የወሰዷቸውን እርምጃዎች ከግምት ያስገባ ነበር።
እስከዚያ ድረስ በእነዚህ አገራት የሞተው ሰው ብዛት 130 ሺህ ብቻ ነው።
ይህ ጥናት ሞዴል ያደረገው የበሽታን የስርጭት ቅርጽ ሲሆን ሰዎች ቤታቸው ቁጭ ባይሉና በእነዚህ አገራት የጉዞ እቀባዎች ባይደረጉ ኖሮ የተህዋሱ የሥርጭት አድማስ የት ይደርስ ነበ? በሚል መላምት የተሠራ ሳይንሳዊ ምርምር ነው።
የቤት መቆየት ግዳጅ፣ የጉዞ እቀባና የአካላዊ መራራቅ ደንብ ተግባራዊ ባይደረግ ኖሮ እስከ ግንቦት 4 ብቻ በአውሮፓ ውስጥ በድምሩ 3 ሚሊዮን 200 ሺህ ሰዎች ይሞቱ ነበር።
ይህ ቡድን ዩናይትድ ኪንግደም ያን ጊዜ በሯን ለመዝጋት በምታቅማማበት ወቅት ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ያቀረበ ቡድን ነው ተብሏል።
ጥናቱ ከሞት የተረፉ ሕዝቦችን ቁጥር በአገራት ደረጃ ከፋፈፍሎ ያስቀመጠ ሲሆን፤ ለአብነትም 470 ሺህ በዩናይትድ ኪንግደም፣ 690 ሺህ በፈረንሳይ፣ 630 ሺህ በጣሊያን ሕይወታቸው ድኗል ብሏል።
የጥናቱ መሪ ዶ/ር ሴዝ ፍላክስማን እንዳሉት ይህ ቤት ዘግቶ የመቀመጥ ነገር ባይኖር ኖሮ ሚሊዮኖች ይሞቱ እንደነበር የሚገነዘበው ሰው ጥቂት ነው።
ጥናቱ ሰዎች በግዳጅ ቤት እንዲቀመጡ ባይደረጉ ኖሮ የባሕሪ ለውጥ አያመጡም ነበር የሚል እሳቤን ይዞ የተነሳ ነው።
ማኅበራዊ መራራቅ ብቻውንም ውጤታማ ላያደርግ እንደሚችልም ግምት ውስጥ ያስገባ ጥናትም እንደሆነ ተመልክቷል።
ቤት ውስጥ መቀመጡ የግድ ባይሆንና መቶ ሺህዎች መሞት ቢጀምሩ ክስተቱ ከሆስፒታሎች ቁጥጥር ውጪ ስለሚሆን የሟቾች ቁጥር እጥፍ ደርብ በሆነ ነበር ሲል ጥናቱ ይደመድማል።
ጥናቱ ሌላው ደረስኩበት ያለው ነገር ሰዎች ቤት ባይቀመጡና ሕይወታቸውን በተለመደው መልኩ ቢቀጥሉ ኖሮ ወረርሽኙ ዛሬ አይኖርም ነበር። ምናልባትም ኮቪድ-19 የሚባል ነገር ያበቃለት ነበር። ምክንያቱም ሚሊዮኖች ስለሚሞቱ ተህዋሱ ሩጫውን ይጨርስ ስለነበረ ነው።
ነገሮች እንደተገመተው ከቁጥጥር ውጪ ቢሆኑ ኖሮ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ከ10 ሰዎች 7ቱ በበሽታው ይያዙ ነበር፤ ይህም ሰዎች የጋርዮሽ በሽታ መከላከል ደረጃ ወይም (ኽርድ ኢሚዩኒቲ) ላይ ይደርሱ ነበር ማለት ነው ብሏል ጥናቱ።
በዚህ ደረጃ አንድ ቫይረስ በሕዝብ ዘንድ ከተሰራጨ ደግሞ ስርጭቱ በራሱ ጊዜ ይገታል።
ይህ ጥናት አሁንም ቢሆን አገራት የጉዞ እቀባና የእንቅስቃሴ ገደብ ካላስቀመጡ ተህዋሱ ሊያንሰራራና በርካታ ሕዝብ ሊጨርስ ይችላል ብሎ ይሰጋል።
ዶ/ር ሳሚር ባት ለቢቢሲ እንደተናገሩት አሁን በሚታየው ሁኔታ ሰዎች ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው ከተመለሱ ቫይረሱ በአዲስ መልክ ሥራ እንደሚጀምር ምንም ጥርጥር የለውም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተመሳሳይ ጥናት በካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ሲሆን ቫይረሱ በቻይና፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በኢራን፣ በፈረንሳይና በአሜሪካ ውስጥ በቆየበት ወቅት የሰዎች እንቅስቃሴ ገደብ ባይጣል ኖሮ በተዘረዘሩት አገራት በቫይረሱ የሚያዙባቸው ሰዎች ቁጥር 350 ሚሊዮን ይሆን ነበር።
ምክንያቱም የእንቅስቃሴ እቀባ ከመደረጉ በፊት የቫይረሱ ስርጭት በተዘረዘሩት አገራት በየሁለት ቀኑ ራሱን እጥፍ እያደረገ ነበር።
የጥናቱ መሪ ዶ/ር ሶሎሞን ሀስያንግ እንደሚሉት ሰዎች ሕይወታቸው የተረፈው ቤት በመቀመጣቸው እንደሆነ ላያውቁት ይችላሉ፤ በአጭር ጊዜ በርካታ ሕይወት ማዳን የተቻለው በእንቅስቃሴ እቀባ እንደሆነ አሁንም ግንዛቤ ያለ አይመስልም።














