ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተነስቶ የነበረው እሣት በቁጥጥር ስር ዋለ
ትላንት [አርብ] በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተነስቶ የነበረው እሣት በቁጥጥር ስር ዋለ።
እሳቱ ትላንት ሳንቃ በር በሚባለው የፓርኩ አካባቢ መከሰቱን የገለጹት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ለምለሙ "አሁን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረነዋል" ሲሉ ለቢቢሲ በስልክ ተናግረዋል።
እሳቱ የተነሳበትን ምክንያት ተጠይቀው አንድ የምርመራ ቡድን ወደ አካባቢው መላኩን እና ውጤቱ እንደታወቀ ይፋ እንደሚያደረግ አስታውቀዋል።
"እሳቱ ሰፊ ጉዳት አድርሷል ተብሎ አይታሰብም" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው "የተወሰነ ሄክታር የሳር መሬት ተቃጥሏል። መጀመሪያ እሳቱ ሲነሳ የአካባቢው ሰው ስለተቆጣጠረው ያን ያህል ጉዳት አደረሰ ለማለት አይቻልም። የኅብረተሰቡ ተከታትሎ ባያጠፋው ኖሮ ጉዳቱ ሰፊ ይሆን ነበር" ብለዋል።
በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ እሳት መነሳቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በሆሌኮፕተር እና ከእስራኤል በመጡ ባለሙያዎች ድጋፍ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
ከዚህ ልምድ በመወስድ በእያንዳንዱ ወረዳ የእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድ መቋቋሙን ያስታወቁት አቶ ወርቁ እሳቱ በተለያየ ምክንያት እንደሚነሳ አስታውቀው "ቆላው ላይ በተፈጥሮ እሳት ሊነሳ ይችላል። ይህ ግን [የትላንቱ] ደጋ ስለሆነ በተፈጥሮ ነው የተነሳው ብሎ ለመደምደም አያስችልምም። ለማንኛውም እየተጠና ነው" ብለዋል።
ከተቋቋመው የእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድ በተጨማሪ የአካባቢው ማኅበረሰብ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው በመደረጉ የዘንድሮው እንደ አምናው ጉዳት አለማድረሱን ገልጸዋል።
በአውሮፓዊያኑ 1978 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ባለፈው ዓመት እሳት ተነስቶ ሰፊ ጉዳት ካደረሰ በኋላ በጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
በዚህም ሳንቃ በር እና መስገጎ በሚባሉ ቦታዎች 330 ሄክታር በላይ ቦታ ተቃጥሎ ነበር።