ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ የሩሲያ ወታደራዊ ቤተ-ክርስቲያን የፑቲንን 'ሞዛይክ' ሊያፈርስ ነው
ሩሲያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወታደራዊ ቤተ-ክርስቲያን ለፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የቀረፀውን የግድግዳ ላይ ምስል [ሞዛይክ] ፕሬዝደንቱ በመቃወማቸው ምክንያት መሰረዙን አስታውቋል።
አጨቃጫቂው ምስል ፕሬዝደንት ፑቲን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ እንዲሁም የፀጥታ ኃላፊውና ሌሎች የሚታዩበት ነው።
ሞስኮ አቅራቢያ የሚገኘው የግዙፉ ቤተ-ክርስቲያን ጳጳስ የግድግዳ ላይ ምስሉ [ሞዛይኩ] በቅርቡ ሊነሳ እንደሚችል አስታውቀዋል።
ሌላኛው ሊፈርስ ይችላል የተባለው ሞዛይክ አንዲት ሴት 'ክሪሚያ የእኛ ናት' የሚል መዝሙር ስታቀነቅን ያሳያል።
ሩሲያ በ2014 [እ.አ.አ.] የክሪሚያ ባሕረ-ሰላጤን ከዩክሬን መነጠሏ አይዘነጋም።
የፑቲን ሞዛይክ ምስል የተሰቀለበት ቤተ-ክርስቲያን ከ75 ዓመታት በፊት ሶቪየት ሕብረት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን በድል ከተወጣች በኋላ የተገነባ ነው።
የቤተ-እምነቱ መግቢያ ከናዚ ወታደሮች በተነጠቁ ዕቃዎች የተሠራ ነው። ነገር ግን የፕሬዝደንት ፑቲን ምስል ግድግዳ ላይ መሳሉ አጨቃጫቂ ሆኖ ነበር። ጉዳዩ አጨቃጫቂ ሆኖ ሲገኝ ክሬምሊን [የሩስያ ቤተ-መንግሥት] ምስሉን ፑቲን አላፀደቁትም የሚል መግለጫ አውጥቷል።
የቤተ-መንግሥቱ ቃል-አቀባይ ጉዳዩ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተደምጠዋል። አልፎም ምስሉ ወዲያው እንደሚነሳ አሳውቀዋል።
ቃል-አቀባዩ አንድ አዲስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚታየው የጆሴፍ ስታሊን ምስል ስለመነሳት አለመነሳቱ ያሉት የለም።
የጆሴፍ ስታሊን ምስል የሚታይበት አዲሱ ቤተ-ክርስቲያን በያዝነው ወር ይመረቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሊራዘም ይችላል ተብሏል።