ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቶማስ ታባኔ: በቀድሞ ባለቤታቸው ግድያ የተወነጀሉት የሌሶቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰራዊት አሰማሩ
በቀድሞ ባለቤታቸው ግድያ የተወነጀሉት የሌሴቶው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ ሕግና ሰላምን ለማስፈን በሚል ሰራዊት አሰማርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገራቸው ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው እንደተናገሩት ሕግ አስፈፃሚዎች የዴሞክራሲን ፅንሰ ሃሳብ እየተፈታተኑት ይገኛሉ ብለዋል።
እነዚህን ህግ አስፈፃሚዎች ግን በስም አልጠቀሱም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማውን የማገድ ውሳኔያቸውን ፍርድ ቤቱ መሻሩን ተከትሎ ነው ሰራዊት ወደማሰማራት የገቡት።
የቀድሞ ባለቤታቸው የተገደሉት ከሶስት ዓመታት በፊት ሲሆን፤ በተደረገው ምርመራ የእሳቸው እንዲሁም የቀድሞ ባለቤታቸው እጅ መኖሩን ተከትሎ ሃገሬው ከስልጣን እንዲለቁ ከፍተኛ ግፊት እያደረገባቸው ነው።
ግድያው እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳትፎ ብዙዎችን አስደንግጧል።
የቀድሞ ባለቤታቸው በሽጉጥ በተገደለችበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የፍች ሂደት ላይ ነበሩ ተብሏል።
ባለቤታቸው ከሞተች ከሁለት ወራት በኋላ ከአዲሷ ባለቤታቸው መሲያህ ጋር ጋብቻን ፈፅመዋል። ባለቤታቸው በተገደለችበት ወቅት ከአሁኗ ሚስታቸው ጋር አብረው ይኖሩ ነበር።
መሲያህም ከግድያው ጋር በተያያዘ ከወራት በፊት ክስ የተመሰረተባት ቢሆንም በዋስ ተለቃለች።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቆች በበኩላቸው ባለስልጣን እንደ መሆናቸው መጠን ያለመከሰስ መብታቸው ይከበር እያሉ ነው።
ጉዳያቸውን የያዘው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ህገ መንግሥታዊ አተረጓጎሙን አይቶ የመከሰስ አለመከስ ሁኔታቸው ላይ የሚወስን ይሆናል።
የ80 አመቱ አዛውንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተደጋጋሚ ከፓርቲው ስልጣን ይልቀቁ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፤ በሀምሌ ወር እለቃለሁ ብለዋል።