ኮሮናቫይረስ፡ "ለ40 ዓመት ካላገኘኋት እህቴ ጋር አብሬ እየኖርኩ ነው"

ታትሟል

ኮሮናቫይረስ የአገራትን እንቅስቃሴ ሲገታ፤ ሱ ብሪምነር እና ባለቤታቸው ዴቪድ ኒው ዚላንድ ነበሩ።

በርካቶችን ሰላም የነሳው ወረርሽኙ ለእነ ሱ ግን በጎ ነገር ይዞ የመጣ ይመስላል።

ሱ፤ ማርጋሬት ሐኒ የምትባል እህት አለቻቸው። ነገር ግን ለ40 ዓመታት ያህል የት እንዳለች አያውቁም ነበር። እንዲያውም እህት እንዳላቸውም የሚያውቁት ነገር አልነበረም።

ማርጋሬት አሁን የ71 ዓመት አዛውንት ናቸው። ለጉዲፈቻ የተሰጡት የሁለት ሳምንት ጨቅላ ሳሉ ነበር። የሱ እናት ከአጋራቸው ጋር ለረዥም ጊዜ አብረው አልቆዩም። ስለዚህም ማርጋሬትን ለማደጎ ሰጡ።

ሱ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ማርጋሬት ደግሞ በኒው ዚላንዷ ኦክላንድ ይኖሩ ነበር።

የ65 ዓመቷ ሱ፤ ከኦክላንድ መልዕክት ሲድርሳቸው፤ የማያቋትን እህት ለመተዋወቅ ወደ ኒው ዚላንድ አቀኑ። ከባለቤታቸው ጋር ወደ ኒው ዚላንድ ሲሄዱ ለሁለት ወር ለመቆየት ወጥነው ነበር።

ኒው ዚላንድ ደርሰው በሁለተኛው ሳምንት ግን በመላ አገሪቱ እንቅስቃሴ እንዲቆም ታዘዘ። ባልና ሚስቱም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የመመለስ እቅዳቸውን ሰረዙ።

ማርጋሬት እና ባለቤታቸው ጆን፤ ከሱ እና ከባለቤታቸው ዴቪድ ጋር በጋራ እየኖሩ ነው።

"ድንቅ ጊዜ እያሳለፍን ነው"

"ብዙ ጊዜያችንን አብረን እናሳልፋለን፤ ወይን እንጠጣለን፣ ምግብ እናበስላለን. . . ድንቅ ጊዜ እያሳለፍን ነው" ሲሉ ሱ ይናገራሉ።

ማርጋሬት በበኩላቸው፤ አንድ ኩሽና ለአራት መጋራት አስቸጋሪ ቢመስልም "እስካሁን አልተጋደልንም" በማለት አብሮነታቸውን ይገልጹታል።

ሱ፤ እህት እንዳላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት ከ20 ዓመት በፊት፣ ወላጅ አባታቸው ከሌላ ሴት የወለደው ልጅ እንዳለው ሲነግራቸው ነበር።

"አባቴ ማርጋሬትን እንድፈልጋት ጠየቀኝ፤ ልጁ ለማደጎ ከተሰጠች በኋላ አንድም ቀን ስለ ልጁ ሳያስብ ውሎ እንደማያውቅ ነገረኝ። ይህንን ማርጋሬትም እንድታውቅ ይፈልግ ነበር" ይላሉ ሱ።

ከዚያም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እህታቸውን መፈለግ ጀመሩ። የቤተሰብ የዘር ሀረግ መረጃ የሚያከማቹ ድረ ገጾችን ያስሱም ነበር።

ማርጋሬት ኒው ዚላንድ መኖር የጀመሩት ከ45 ዓመት በፊት ነበር። የጉዲፈቻ ልጅ እንደሆኑ ቢያውቁም ቤተሰቦቻቸውን ለረዥም ጊዜ የመፈለግ እቅድ አልነበራቸውም።

አምና ግን ሐሳባቸውን ቀየሩ። ቤተሰቦቻቸውን እየፈለጉ መሆኑንም ለልጃቸው ነገሩ።

ፍለጋ በጀመሩ በሁለት ሳምንት ውስጥ የእህታቸውን አድራሻ አገኙ።

"አልጋ ውስጥ ሆኜ ሻይ እየጠጣሁ ነበር። ባለቤቴ ጆን ከጎኔ ተኝቶ ያንኮራፋ ነበር። አንድ ኢሜል ስከፍት እህት እንዳለኝ አወቅኩ። ባለቤቴ ሲነቃ ሻዬን ይዤ ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ ነበር" ሲሉ ማርጋሬት እህታቸውን ያገኙበትን ቅጽበት ያስታውሳሉ።

ጊዜ ሳያጠፉ ለእህታቸው ሱ ኢሜል ላኩ። አባታቸው የልጆቹን መገናኘት ሳያይ ቢሞትም፤ እህትማማቾቹ ለመገናኘት ወሰኑ።

"ብዙ የሚያመሳስሉን ነገሮች አሉ"

ማርጋሬትና ሱ፤ ሎረንስ እና ጆን የሚባሉ ወንድሞች አሏቸው። አራቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት አምና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ነበር።

"ከቤተሰብ ጋር መገናኘት እጅግ አስደሳች ነው፤ ብዙ የሚያመሳስሉን ነገሮች አሉ" ይላሉ ማርጋሬት።

ሱ እና ማርጋሬት ለስላሳ ቡና ይወዳሉ። ሁለቱም ጉልበታቸውን ያማቸዋል።

ኮሮናቫይረስ ከተቀሰቀሰ በኋላ፤ ከኒው ዚላንድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሊደረጉ የነበሩ ሁለት በረራዎች በመሰረዛቸው ሱ እና ባለቤታቸው ወደ አገራቸው መመለስ አልቻሉም።

በሚቀጥለው ቅዳሜ የመመለስ እቅድ ቢኖራቸውም ሀኪም ልጃቸው ኒው ዚላንድ እንዲቆዩ መክራቸዋለች።

ኒው ዚላንድ ውስጥ እስካሁን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሞተው አንድ ሰው ብቻ ነው። ልጃቸውም ይህን እውነታ በማጣቀስ ባላችሁበት ቆዩ ብላቸዋለች።

እህትማማቾቹ በዚህ ዓመት መጨረሻ በዩናይትድ ኪንግደም በድጋሚ ለመገናኘት አቅደው ነበር። አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ግን እቅዳቸውን ወደፊት ለመግፋት ተገደዋል።

"ካሁኑ በድጋሚ ስለምንገናኝበት ጊዜ እያቀድኩ ነው፤ ሁሉንም ቤተሰብ ሰብስቤ ሉልዶው ቤተ መንግሥት መውሰድ እፈልጋለሁ" ሲሉ የወደፊት እቅዳቸውን ሱ ይገልጻሉ።