ኮሮናቫይረስ፡ የንግሥቲቱ የቴሌቪዥን ንግግር 24 ሚሊዮን ሰዎች በቀጥታ ተመልክተውታል

የንግሥት ኤልሳቤጥ 2ኛ

የፎቶው ባለመብት, Buckingham Palace

ታትሟል

የታላቋ እንግሊዝ፣ የሰሜን አየርላንድ በጠቅላላው ዩናይትድ ኪንግደምና የኮመንዌልዝ ሌሎች ግዛቶች ንግሥት የዳግማዊት ኤልዛቤጥን የእሑዱን ንግግር 24 ሚሊዮን ሰዎች በቀጥታ ተመልክተውታል።

ይህ በብዙ ዓመታት አንዴ የሚደረግ ነው የሚባልለት የንግሥቲቱ ሕዝባዊ ንግግር ዓለማቀፍ ትኩረትን ስቦ ነበር።

ግርማዊት ኤልሳቤጥ 2ኛ በንግግራቸው ሕዝባቸው ከመንግሥት የሚወጡ መመሪያዎችን 'እህ' ብሎ ሰምቶ ተግባራዊ በማድረጉ አመስግነዋል።

የንግሥቲቱ ንግግር በዚህ ዓመት በርካታ የቴሌቪዥን ተመልካቾችን ትኩረት ከሳቡ ሕዝባዊ ንግግሮች 2ኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከመታመማቸው በፊት በኮረናቫይረስ ወረርሽኝ ዙርያ ያስተላለፉት መልእክት 27 ሚሊዮን ሰዎች ተመልከተውት ነበር።

የግርማዊት ንግሥቲቱን ንግግር በቢቢሲ - 1 ጣብያ ብቻ 14 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል፤ 5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በአይቲቪ እንዲሁም 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በቻናል 4 እና 5 እንዲሁም ቀሪዎቹ በስካይ ኒውስ መመልከታቸው ተዘግቧል።

ዳግማዊት ኤልዛቤጥ በ68 ዓመት ንግሥናቸው ሕዝባዊ ንግግር ሲያደርጉ ይህ ለ5ኛ ጊዜ ብቻ ነው።

በእሑድ ምሽቱ ንግግራቸው ንግሥቲቱ ኮሮናቫይረስን ድል እናደርገዋለን፤ ዳግም በሰላም እንገናኛለን፤ ዳግም ከቤተቦቻችን ጋር እንቀላቀላለን፤ ሁሉም መልካም ይሆናል፤ አይዟችሁ ሲሉ ተስፋ የተሞላበት ንግግር ነበር ያደረጉት።

ንግሥቲቱ በተለይ ላቅ ያለ ምሥጋና ያቀረቡት ለአገራቸው ጤና ባለሙያዎች ነው።

ቀደም ያሉት ቀሪዎቹ የግርማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሕዝባዊ ንግግሮች የተደረጉት እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ የጊዜ ቀመር በ1991፣ 1997፣ 2002 እና 2012 ላይ ነበር።

የመጀመርያው ንግግራቸው በኢራቅ ጦርነት መባቻ ላይ የተደረገ ሲሆን ሁለተኛው የልዕልት ዲያናን ሞት ተከትሎ የሆነ ነው።

ይህ የክቡርነታቸው የንግሥት ኤልዛቤት 2ኛ ንግግር በቀጥታ የተደረገ ሳይሆን ቀደም ብሎ የተቀረጸ ነው። ለቀረጻውም አንድ የካሜራ ባለሞያ ብቻ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን ባለሞያውም ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግና ሙሉ የቫይረስ መከላከያ በማጥለቅ እንዲሁም ከንግሥቲቱ ተገቢውን ርቀት ጠብቆ እንዲቆም መደረጉ ተዘግቧል።

ክቡርነታቸው ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤት የተወለዱት እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1926 ነው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ 94ኛ ዓመታቸውን ያከብራሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም ታሪክ የንግሥቲቱ የንግሥና ዘመን በርዝመቱ ወደር የማይገኝለት ነው።

ኮሮና