ኮሮናቫይረስ፡ ሲንጋፖር ከ20ሺህ በላይ የውጪ አገር ሰራተኞችን በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስቀመጠች

ከውጪ አገር የመጡ ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሲንጋፖር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ በመምጣቱ 20 ሺህ የውጭ አገር ሠራተኞች በማደሪያ ክፍላቸው ውስጥ ለ14 ቀናት እንዲቆዩ አዘዘች።

እነዚህ ሠራተኞች የህንድ፣ የታይላንድ፣ የስሪላንካና የባንግላዲሽ ዜግነት ያላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ሠራተኞቹ በሁለት የተለያዩ ህንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን 13 ሺህ ሠራተኞች ያሉበት አንዱ ማደሪያ ውስጥ ብቻ 63 በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 6800 ሠራተኞች ባሉበት የማደሪያ ሕንፃ ደግሞ 28 ታማሚዎች ተገኝተዋል።

የሲንጋፖር መንግሥት ወደ እነዚህ ሁለት የመኖሪያ ህንፃዎች ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ሲል የእንቅስቃሴ ገደብ አስቀምጧል።

እነዚህ ህንጻዎች ከደቡብ እስያ ለሚመጡ የግንባታ ሠራተኞች ማደሪያ በመሆን የሚያገለግሉ ናቸው ተብሏል።

ሠራተኞቹ በክፍላቸው ለአስራ አራት ቀን ሲቆዩ ክፍያቸው የማይቋረጥ ሲሆን በቀን ሦስቴ እንዲመገቡ ይደረጋል ተብሏል። የሠራተኞቹን ደሞዝ አሰሪያዎቻቸው የሚሸፍኑ ሲሆን የምግባቸውንም ወጪ እንዲችሉ ተደርጓል ተብሏል።

ነገር ግን ክፍሎቹ በሰው ብዛት መጨናነቃቸውና ንጽህናቸው አለመጠበቁን አንስተው የሚተቹ አልጠፉም።

ነዋሪዎቹም ቢሆኑ እነዚህ ማደሪያዎች የንጽህና ክፍላቸው የሚያፈስ፣ ምግብ ለማግኘት ረዣዥም ሰልፍ የሚደረግባቸውና በበረሮ የተሞሉ መሆኑን ይናገራሉ።

በሲንጋፖር ፑንጎልና ዌስቲት የሚገኙት እነዚህ ማደሪያዎች ሙሉ በሙሉ መውጣትና መግባት ተከልክሎባቸዋል።

ኮሮና
Banner

መንግሥት እንዳለው በእነዚህ ማደሪያ ህንጻዎች የሚገኙ ታማሚዎች ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል።

እናም ቤት የመቆየት ገደቡ "የሠራተኞቹን ደህንነት ለመጠበቅና ስርጭቱ ወደ ማኅበረሰቡ እንዳይስፋፋ ለመከላከል የተደረገ" ነው ብሏል።

ሠራተኞቹ የሚኖሩበትን ፎቅ ለቅቀው መውጣት የማይችሉ ሲሆን በክፍላቸው አልያም በፎቃቸው ላይ ከማይኖሩ ሰዎች ጋርም እንዳይቀላቀሉ ተነግሯቸዋል።

በአንድ ክፍል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከክፍል ክፍል ይለያል ተብሏል።

ቢቢሲ በ2015 ባደረገው ጉብኝት በአንድ ክፍል ውስጥ 12 ሰዎች እንደሚኖሩ ተመልክቷል።

ለሠራተኞቹ ከምግባቸው በተጨማሪ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ሙቀታቸውን መለኪያ ቴርሞ ሜትር ይሰጣቸዋል ተብሏል።

ሠራተኞቹ በቀን ሁለቴ ሙቀታቸውን መለካትና መመዝገብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በመኖሪያ ህንፃቸው አቅራቢያ የህክምና ቡድን እንደሚኖር ተገልጿል።

ሲንጋፖር ከውጪ አገር መጥተው ለሚሰሩ ሠራተኞች ማደሪያ በግለሰቦች የሚዘጋጅ ሲሆን ከ1ሺህ በላይ ነዋሪዎች ካሉ በመንግሥት ተመዝግቦ ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል።

በአጠቃላይ በአገሪቱ ከ40 በላይ የሠራተኞች ማደሪያዎች ይገኛሉ።

በሲንጋፖር እስካሁን ድረስ 1300 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲታወቅ ስድስት ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

በዚያች ትንሽዬ አገር ውስጥ 5.7 ሚሊዮን ሕዝብ ሲኖር ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1.4 ሚሊዮኑ ከውጪ አገራት የመጡ ሠራተኞች ናቸው።