በቻይና በተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ የሠራተኞች ሕይወት አለፈ

ታትሟል

በቻይና ሲሹዋን ግዛት፤ በጫካ ውስጥ የተቀሰቀሰ እሳት ለማጥፋት ተሰማርተው የነበሩት 8 የእሳት አደጋ ሠራተኞች እና መሪያቸው መሞታቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

ዥንዋ የዜና ወኪል እንዳለው ግለሰቦቹ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት የነፋስ አቅጣጫ በመለወጡ መውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል።

እሳቱ በአንድ የእርሻ መሬት ላይ ትናንት የጀመረ ሲሆን፤ በወቅቱ የነበረው ኃይለኛ ነፋስ በቅርብ ወደሚገኝ ተራራ እንዲዛመት አድርጎታል።

እሳቱን ለመቆጣጠር ሲጥሩ ሕይወታቸውን ያጡት የእሳት አደጋ ሠራተኞች፤ መሪያቸው የነበረን አንድ የእርሻ ሠራተኛን ያካተተ 22 አባላት ያሉት ቡድን አካል ነበሩ።

ከአደጋው የተረፉ ሦስት ሠራተኞች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ተብሏል።

እሳቱ በአሁኑ ጊዜ ወደ 1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዛመተ ሲሆን ከ2 ሺህ በላይ የእሳት አደጋ እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ ስፍራው ተልከዋል።

1 ሺህ 200 የሚሆኑ ነዋሪዎችም አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል።

ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ አደጋ ያጋጠመ ሲሆን እሳቱን ለመቆጣጠር በተደረገው ሂደት 30 የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።