በኮሮናቫይረስ እየተናጠች ያለችው የጣሊያኗ ሎምባርዲ ግዛት ጥብቅ እገዳ ጣለች

ታትሟል

በጣሊያን ኮሮናቫይረስ የተቀሰቀሰባትና በቫይረሱ ክፉኛ እየተፈተነች ያለችው የሎምባርዲ ክልል ነዋሪዎች ከቤታቸው በምንም ምክንያት መውጣት እንደማይችሉ አስታወቀች።

ሳምንታዊ የጎዳና ላይ ሰፋፊ ገበያዎችም ታግደዋል።

ግዛቲቱ ትናንት ከሰዓት በኋላ ያወጣችው መመሪያ ነዋሪዎች ለግል ስፖርታዊ እንቅስቃሴም ሆነ ለአካል ብቃት ከቤታቸው ወጣ ማለትን ይከለክላል።

ይህ ክልከላ በትናንትናው ዕለት ብቻ ጣልያን 800 የሚሆኑ ሰዎችን በኮሮናቫይረስ ማጣትዋን ተከትሎ ነው።

በአገሪቱ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 4825 በመድረስ የዓለም ከፍተኛው የኮሮናቫይረስ ሞት ሆኖ ተመዝግቧል።

ጥብቅ መመሪያ በማውጣት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ጎዳናዎቿ ላይ ወታደሮች ያሰማራችው የሎምባርዲ ከዚህ ሞት 3095 የሚሆነው የተመዘገባት የጣልያን ክልል ነች።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቲሊዮ ፎንታና በመግለጫቸው እንዳስታወቁት ከሆስፒታል፣ ከመንገድና ባቡር ትራንስፖርት ባሻገር በክልሉ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደማይኖር ገልፀዋል።

ሎምባርዲ ክልል ላለፉት ሁለት ሳምንታት በላይ ማንም የማይወጣባትና የማይገባባት ክልል ሆና ቆይታለች። ትናንት የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ዘርዝራቸውን ብለው ባይለዩም የንግድ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በአገሪቱ ይቋረጣሉ ብለዋል።

ሱፐርማርኬቶች፣ ፋርማሲዎች፣ ፖስታ ቤት እና ባንኮች ግን ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ ገልፀዋል። በተመሳሳይ የሕዝብ ትራንስፖርቶችም እንዲሁ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

"የአገሪቱን የምርት ሞተር እናቀዘቅዘዋለን እንጂ ጨርሶ አናቆመውም" በማለት መቀጠል የሚገባቸው ነገሮች መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ250 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ሞቶቹም ከ10 ሺህ በላይ ሆነዋል።