የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤቱን መሰረዙን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ይግባኝ ሊጠይቁ ነው.

የፎቶው ባለመብት, AMOS GUMULIRA
የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤቱን መሰረዙን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ይግባኝ ሊጠይቁ ነው።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን አወዛጋቢ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት መሰረዙን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ እንደማይቀበሉትና ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።
የፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚቃወሙትና ይህንንም ለማሳወቅ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ነው።
በግንቦት ወር በተካሄደው ምርጫ ፒተር ሙታሪካ 38 በመቶ ድምፅ በማግኘት የማላዊ ፕሬዚዳንት መሆናቸው ይፋ ቢሆንም፤ ሰኞ እለት ነበር በምርጫው ላይ ከፍተኛ ማጭበርበሮች ነበሩ በማለት ውጤቱ በዳኞች ውድቅ የተደረገው።
የሃገሪቱ ፍርድ ቤትም ባሳለፈው ውሳኔ በ150 ቀናት ውስጥ አዲስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ማላዊን የሚያስተዳድረው የዴሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ደጋፊዎቻቸው እንዲረጋጉ መልዕክት አስተላልፏል።
የተፎካካሪው መሪ ላዛሩስ ቻክዌራ በሺዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ውሳኔው ለዲሞክራሲ ድል ነው ብለዋል።
ላዛሩስ ቻክዌራ በምርጫውም 35 በመቶ ድምጭ በማግኘት ፒተር ሙታሪካን እየተከተሉ የነበረ ሲሆን ምርጫው ተጭበርብሯልም በሚል ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስደውት ነበር።
በጎርጎሳውያኑ 2017 የኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ከተሰረዘ በኋላ ማላዊ ተመሳሳይ ውሳኔ በማሳለፍ ሁለተኛዋ ከሰሃራ በታች የምትገኝ አገር ሆናለች።












