"እየሩሳሌም የማትከፋፈል የእስራኤል ዋና ከተማ ናት" ዶናልድ ትራምፕ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰላም ለራቀው መካከለኛው ምሥራቅ እጹብ ድንቅ የሆነ እቅድ ይዣለሁ ሲሉ ነበር የከረሙት። ይህን 'የዘመኑ ታላቅ የሰላም እቅድ' ይፋ ያደረጉት ግን ትናንት ምሽት በቤኒያምን ናታንያሁ ታጅበው ነው።

የፍልስጤሙ አባስ ጭራሽ በቦታውም አልነበሩም። ፍልስጤማዊያኑን የሚወክል አካልም በቦታው አልታየም። ምናልባት የኦማንና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተው ሊሆን ይችላል።

ይህ ብዙዎች ለእስራኤል ያደላ ነው ያሉት 'የክፍለ ዘመኑ የሰላም እቅድ' የዓለምን ትኩረት ስቦ ነው ያመሸው።

የዶናልድ እቅድ ነጻ የፍልስጤም አገርን የሚፈቅድ ቢሆንም ለእስራኤልን ህገ ወጥ ይዞታዎች በስፋት እውቅና የሚሰጥ ሆኗል።

ትራምፕ "ይህ እኔ ያመጣሁት እቅድ ካልሰራ ሌላ ምንም ነገር ሊሰራ አይችልም' ብለዋል።

የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ "አሻጥር" ሲሉ የሰላም ሰነዱን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገውታል።

የሰነዱን ይፋ መሆን ተከትሎ ፕሬዝዳንት አባስ ከራማላህ ባደረጉት የቴሌቪዥን ንግግር "ለትራምፕና ናታንያሁ የምለው አለኝ፤ እየሩሳሌም ለገበያ አትቀርብም፥ መብቶቻችን ለሽያጭ አይቀርቡም" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን እንዲሉ ያበቃቸው ትራምፕ በምጣኔ ሐብት ለተንኮታኮተችው ፍልስጤም በታሪኳ አይታም ሰምታም የማታውቀው የኢንቨስትመንት ገንዘብ እንሰጣታለን ማለታቸው ነው። ይህም በድምሩ 50 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል።

ይህንን 'የክፍለ ዘመኑን የሰላም ሰነድ' በበላይነት ሲያረቁ ከነበሩት ዋንኛው የትራምፕ ሴት ልጅ የኢቫንካ ትራምፕ ባል ጄርድ ኩሽነር ነው።

የሰላም ሰነዱን ይፋ መሆን ተከትሎ በበርካታ የአረብ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ እቅድ የተደረገ ሲሆን በጋዛ ሰርጥ ፍልስጤማዊያን የትራምፕን ምሥል ሲያቃጥሉ አድረዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እቅዱ በዚህ ወቅት ይፋ መሆኑ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ይላሉ።

ዶናልድ ትራምፕ በሴኔት እየታየ ያለው ክሳቸውን ለማደባበስ፣ ናታንያሁ ደግሞ በእስራኤል ያለባቸውን የሙስና ክስ ትኩረት እንዲነፈገው ብሎም ጥምር መንግሥት ለመመሥረት ባለመቻላቸው በመጪው ምርጫ በቀላሉ ተቀናቃኛቸውን ድል ለመንሳት ሁነኛ ሰዓት መርጠው ነው እቅዱን ይፋ ያደረጉት የሚሉ ተንታኞች አልጠፉም።

በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ፍሪድማን ግን በዚህ አይስማሙም።

'እቅዱ ይፋ የሆነበት ወቅት ከምንም ፖለቲካዊ ኩነት ጋር የሚያያዝ አይደለም። በዚህ እቅድ ዙርያ ለረዥም ጊዜ ስንሰራ ነው የቆየነው' ብለዋል።

እቅዱ ለእስራኤል ያደላ ነው ካስባሉት ጉዳዮች መሀል በዌስት ባንክ የእስራኤልን ሕገ ወጥ ይዞታዎች ሕጋዊ ማድረጉ ነው።

እስራኤል በኃይል በያዘቸው ዌስት ባንክ ይዞታዎች ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ እስራኤላዊያን ቤት ሠርተው ይኖራሉ። ዌስት ባንክ በዓለማቀፍ ሕግ እስራኤል በሕገወጥ ወረራ የያዘችው እንደሆነ ነው የሚታሰበው። አውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የዓለማቀፉ ማኅበረሰብም በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩነት የለውም።

ይህ የክፍለዘመኑ ሰነድ ምን ይዟል?

ሰነዱ በአጭሩ የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦችን ያነሳል፤

  • አሜሪካ የእስራኤልን ሉአላዊነት እስራኤል በቀጣይ በምትይዛቸው ይዞታዎች ጭምር ታረጋግጣለች።
  • የፍልስጤም ግዛት አካል የሚደረጉ ብጥስጣሽ መሬቶች ይኖራሉ። ፍልስጤም እንደ አገር ስትቆምም በምሥራቃዊ እየሩሳሌም ዋና ከተማ ይኖራታል። አሜሪካም ኤምባሲዋን እዚያ ትከፍታለች።
  • እየሩሳሌም በፍጹም የማትከፋፈልና ለድርድር የማትቀርብ የእስራኤል ዋና ከተማ ትሆናለች።
  • ማንኛውም ፍልስጤማዊም ሆነ እስራኤላዊ ከቤቱ አይፈናቀልም። ይህም ማለት በዌስት ባንክ ህገ ወጥ ሰፈራዎች ሕጋዊ የእስራኤል ግዛቶች ሆነው ይቀጥላሉ።
  • እስራኤል በዮርዳኖስ ንጉሥ የበላይ ጠባቂነት የቅድስት እየሩሳሌምን መንፈሳዊ ስፍራዎች መስጂድ አል አቅሳን ጨምሮ በጥምረት ያስተዳድራሉ። ቅዱሳን ቦታዎችም ለማንኛውም ዜጋ ክፍት ይደረጋሉ።
  • ለፍልስጤም የተሰጡ ይዞታዎች ለአራት ዓመታት ያህል ከማንኛውም የእስራኤል የግንባታ እንቅስቃሴዎች ነጻ ተደርገው ይቆያሉ። በዚህ ወቅትም ፍልስጤም ይህን የሰላም አቅድ አስባበት፣ ከእስራኤል ጋር ድርድር እንድትጀምር እና አገር እንድትመሰርት ይጠበቃል።

80 ገጽ የያዘው እቅድ ትናንት ምሽት በዋይት ሃውስ ይፋ ሲደረግ ከፍተኛ የእስራኤልና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

እቅዱ ከገዛ መሬታቸው ተፈናቅለው እስከዛሬም በስደት በተለያዩ አገሮችና በስደተኛ መጠለያ ካምፖች ጭምር አስቸጋሪ ሕይወትን የሚገፉ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማዊያን፣ ወደ ትውልድ ቀያቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ የሚለው ነገር ስለመኖሩ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም።

ፍልስጤማዊያን አሜሪካ በፍልስጤምና በእስራኤል መሀል ሀቀኛ አደራዳሪ የመሆን የሞራል ልእልና የላትም ይላሉ።

ይህም በታሪክ በተደጋጋሚ የታየ ሐቅ እንደሆነ ሲያስረዱ የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ጭምር በመጥቀስ ነው።

አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ማዘዋወሯና ለፍልስጤማዊያን በተለያየ መንገድና ድርጅቶች ይደርስ የነበረ በሚሊዮኖች ዶላር የሚገመት ገንዘብ ፈሰስ እንዳይደረግ ማገዷ ይጠቀሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የጎላን ኮረብታዎችን የእስራኤል ሉአላዊ ግዛቶች አድርጋ መቀበሏ አሜሪካ በፍጹም ሐቀኛ አደራዳሪ ሊያደርጋት አይችልም ብለው የሚከራከሩ አሉ።

በዚህ የሰላም እቅድ የመሪነት ሚና የነበረው ትራምፕ አማቹ የሆኑት ሚስተር ኩሽነር "ይህ እቅድ ለፍልስጤም የመጨረሻው የሰላም እድል ነው፤ ፍልስጤማዊያን ያለፈ ተረት ተረታቸውን እርግፍ አድርገው ሊተዉት ይገባል" ሲል አስጠንቅቋል።

ይህ እቅድ ይፋ ሲሆን ከዶናልድ ትራምፕ ጎን ዋይት ሃውስ የነበሩት ቤንያሚን ናታንያሁ በእስራኤል ታሪክ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ውለታ የዋለ ፍጡር አላየሁም ሲሉ ደጋግመው አሞካሽተዋቸዋል።

'እስራኤል እንደርስዎ ያለ ወዳጅ፣ እንደ አሜሪካ ያለ ኃያል መንግሥት ከጎኗ በመኖሩ ተባርካለች' ብለዋል ቤንጃሚን ናታንያሁ።