ተሰርቆ የነበረው ባለ 66 ሚሊዮን ዶላር ሥዕል ከ 23 ዓመታት በኋላ ተገኘ

በእውቁ ኦስትሪያዊ ሠዓሊ ጉስታቭ ክሊምት የተሳለው የሴት ሥዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሴትዮዋ ገፅ የተሳለው ከአውሮፓዊያኑ 1916-17 ባለው ጊዜ ነው
ታትሟል

የእውቁ ኦስትሪያዊ ሰዓሊ ጉስታቭ ክሊመት ወጥ ሥራ የሆነው ሥዕል ከተሰረቀ ከ23 ዓመታት በኋላ ባለፈው ወር መገኘቱን የጣሊያን ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

የአንዲትን ሴት ገፅታ የሚያሳየው ይሄው ሥዕል በፒያሴንዛ ሰሜናዊ ከተማ ከሚገኝ ጋለሪ የተሰረቀው በፈረንጆቹ 1997 ነበር።

ለዓመታት ተሰውሮ የቆየው ሥዕሉ አትክልተኞች የጋለሪውን ውጫዊ ግድግዳ ሸፍኖት የነበረውን ሐረግ ሲያጸዱ በግድግዳ ውስጥ በነበረ ክፍተት ውስጥ በሻንጣ ውስጥ ሆኖ ሊገኝ ችሏል።

እንደጠፋ የታመነው ሥዕል በግድግዳው ውስጥ የመገኘቱ ዜና አሁንም ትንግርት ነው ያለው ፖሊስ፤ ምናልባት ተሰርቆ ከተወሰደ በኋላ በድጋሚ ወደዚህ ቦታ ተመልሶ ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምት መኖሩም ተጠቁሟል።

ሥዕሉ በትንሹ 66 ሚሊየን ዶላር ዋጋ እንደሚያወጣ ተነግሮለታል።

የሴትዮዋ ምስል የተሳለው በአርቲስቱ ጉስታቭ ክሊምት የሕይወት መጨረሻ ጊዜ አካባቢ ከአውሮፓዊያኑ 1916 -17 ባሉት ጊዜያት ነው።

ከዚያም በጊዩሴፔ ሪሲ ኦዲ በ1925 ተገዝቶ፤ ለአንድ አውደ ርዕይ ለዕይታ በቀረበበት ጊዜ ተሰርቆ ከተወሰደበት በኋላ ሥዕሉ ጠፍቷል ተብሎ ታምኗል።

ባለፈው ታህሳስ ወር ታዲያ አትክልተኞች በብረት ከተሠራው የጋለሪው ገድግዳ ላይ አትክልቱን እያፀዱ ሳለ ነበር ሥዕሉን የያዘውን አንድ ጥቁር ሻንጣ ያገኙት።

አቃቤ ሕግ ኦርኔላ ቺካ፤ ሥዕሉ ከተሰረቀ ጀምሮ እዚያው ግድግዳው ውስጥ ነበር? ወይስ ኋላ ላይ ነው እንዲመለስ የተደረገው የሚለው ሌላ ተጨማሪ ምርመራ ግልፅ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሥዕሉ ለእይታ እንደሚቀርብም ተናግረዋል።