የማልታው ጉምቱ ባለሃብት በጋዜጠኛዋ ግድያ ተከሰሱ

ሰላማዊ ሰልፈኞች የጋዜጠኛዋን ፎቶ ይዘው

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የማልታው ባለሃብት ዮርገን ፌንች የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ መኪናዋ ውስጥ በተጠመደ ቦምብ በተገደለችው የምርመራ ጋዜጠኛ ዳፍኒ ካሩዋና ጋሊዚያ ግድያ ክስ ተመሰረተባቸው።

ባለሃብቱ ከሌሎች አራት ተጠርጣሪዎች ጋር የቀረበባቸውን ክስ አልተቀበሉም። የወንጀለኛ ቡድን አባል እንደሆኑ የቀረበባቸውንም ክስ በተመሳሳይ ሳይቀበሉ ቀርተዋል ባለሃብቱ።

የምርመራ ጋዜጠኛዋ ዳፍኒ ካሩዋና ጋሊዚያ ግድያ የደሴቲቱ ማልታን መንግሥት እየናጠ ያለ ጉዳይ ሆኗል። የማልታ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ሙስካት ከስልጣን እንዲለቁ ጫና እየተደረገባቸውም ነው።

ቀኝ እጃቸውና አማካሪያቸው የሆኑት ኬዝ ሼምብሪ ባለፈው ሳምንት ከጋዜጠኛዋ ግድያ ጋር በተያያዘ በፖሊስ መመርመራቸውን ተከትሎ ከሃላፊነት ተነስተዋል።

ዮርገን ፌንች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የቱሪዝም ሚኒስትሩ ኮንራድ ሚዚም ስልጣናቸውን ሲለቅቁ የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ክሪስ ካርዶናም ነገሮች እስኪጣሩ ራሳቸውን ከስልጣን እንሚያግዱ አስታውቀዋል።

የካሩና ጋሊዚያን መኪና በቦምብ በማፈንዳት የተጠረጠሩ ሶስት ተጠርጣሪዎች የክስ ሂደት በመሰማት ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ግን ፖሊስ ትኩረቱን ግድያውን ያዘዘው ማን ነው? ለምንስ? የሚለው ላይ አድርጓል።

ባለሃብቱ ዮርገን ፌንች በጋዜጠኛዋ ግድያ በተደጋጋሚ ምርመራ ሲደረግባቸው የቆዩ ሲሆን ከጥቂት ቀናት በፊት በጀልባ ከማልታ ሊወጡ ሲሞክሩ ተይዘዋል። ምህረት የሚደረግላቸው ከሆነ የሚያውቁትን መረጃ ሁሉ እንደሚሰጡ ቢያስታውቁም መንግሥት ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አድርጎታል።