ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋና ውስጥ ለ8 ቀናት የጣለው ዝናብ ከ20 በላይ ሰዎችን ገደለ
በሰሜን ምሥራቅ የጋና ግዛት ውስጥ ለስምንት ቀናት በጣለው ወጀብ የቀላቀለ ዝናብን ተከትሎ ቢያንስ የ28 ሰዎች ህይወት ሲጠፋ በርካታ ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ደረሰ።
ለቀናት በጣላው በዚህ ከባድ ዝናብ ከአንድ ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች የወደሙ ሲሆን በርካታ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
የአካባቢው ባለስልጣናት እንደሚሉት በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር አሁን ከተገለጸው በላይ ሊሆን እንደሚችል ስጋት አላቸው።
የጋና ብሔራዊ የአደጋ መቆጣጠር ድርጅት በከባድ ዝናቡ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እንደጀመረ አሳውቋል።
"ስላለው ሁኔታ አሁን ያለን መረጃ እንደሚያመለክተው በሰሜን ምሥራቅ የጋና አካባቢ ከዝናቡ ጋር ተያይዞ 28 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 140 ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል። ዝናቡ አሁንም እንደቀጠለ ነው" ሲሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጆርጅ አይሳ ተናግረዋል።
ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በአብያተ ክርስቲያናትና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
የጋና ሜቲዮሮሎጂ መስሪያ ቤት ያወጣው የአየር ሁኔታ ትንበያ እንደሚያመለክተው በቀጣዮቹ ሳምንታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ለከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖርና ተጨማሪ የጎርፍ አደጋም ሊያጋጥም እንደሚችል አሰጠንቅቋል።
የእርዳታ ድርጅቶች በዝናቡና ተከትሎት በተከሰተው ጎርፍ ለተጎዱ ሰዎች ተጨማሪ እርዳታ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።