የሱዳን ስደተኞች ቡድን የፈረንሳዩን ባንክ በዘር ጭፍጨፋ ሊከስ ነው

ታትሟል

የሱዳን ስደተኞች ቡድን ቢኤንፒ ፓሪባስ የተባለውን የፈረንሳይ ባንክ በሱዳን ዘር ጭፍጨፋ ላይ ሚና ነበረው በሚል ፍርድ ቤት ሊያቆመው ነው።

ሱዳን በነበረው የዘር ጭፍጨፋ ጥቃት ደርሶብናል የሚለው ይህ ቡድን ባንኩ መንግሥት የፈፀማቸውን ግፎችም ሲደግፍ ነበር በማለት በዛሬው ዕለት ፖሪስ በሚገኘው ፍርድ ቤት የሚያቆሙት።

መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት ሃያ አንዱ ስደተኞች ባንኩ ኒውዮርክ በሚገኘው ቅርንጫፉ በሱዳን መንግሥት የተፈፀሙ ግድያዎችን፣ መደፈር፣ ስቃይ እንዲሁም ሆን ብሎ የኤችአይቪ ቫይረስን ማስተላለፍ ግፎች ላይ ሚና በመጫወትና ህገወጥ የሆኑ የገንዘብ ዝውውሮችን ሂደት በማቀላጠፍ ወንጅለውታል።

በሱዳን ላይ የተፈፀመውን የዘር ጭፍጨፋ ላይ ከተወነጀሉ የመጀመሪያ አለም አቀፍ ድርጅቶች አንዱ ነው።

ከሳሾቹ የፈረንሳይ ዳኞች በባንኩ ላይ የወንጀል ምርምራ እንዲከፈት የጠየቁ ሲሆን ይህም ባንኩን ወይም በባንኩ ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ያለ ሰው ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ፣ እስር እንዲሁም ማዕቀብ ሊጣልበት እንደሚችልም ተጠቁሟል።

ከጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ2002-2008 ባሉት ጊዜያት የሱዳን ባንክ ተብሎ የሚጠራው ይህ ባንክ በአሜሪካ፣ በተባበሩት መንግሥታትና በአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ ማዕቀብ በተጣለበት ጊዜም ለአልበሽር መንግሥት የባንክ አገልግሎት በዋነኝነት ይሰጥ ነበር ተብሏል።

በዚህም ወቅት ዳርፉር ላይ ከፍተኛ ግድያዎች የደረሱ ሲሆን የአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤትም የዘር ጭፍጨፋ ተፈፅሟል ይላል።

የኢኮኖሚ ማዕቀቡን በመጣስ ከሱዳን፣ ከኢራንና ኪዩባ ጋር የገንዘብ ግንኙነት በመፍጠር በአሜሪካ 8.9 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል።