ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዲጄ አረፋት አድናቂዎች በቀብሩ ስርአት ላይ የሬሳ ሳጥኑን በመክፈታቸው አለመረጋጋት ተፈጠረ
ከሰሞኑ በአደጋ ህይወቱ ያለፈው የአይቮሪኮስቱ ታዋቂ ሙዚቀኛ ዲጄ አረፋት ቀብር ላይ የአርቲስቱ አድናቂዎች የሬሳ ሳጥኑን በመክፈታቸው አለመረጋጋት ተፈጥሯል።
የ33 አመቱ ዲጄ አረፋት ወይም አንጂ ዲዲየር የሞተው በሞተር አደጋ ነው።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣ ቪዲዮ እንደሚያሳየው አድናቂዎቹ የሬሳ ሳጥኑን ከፍተው ልብሱንም በማውለቅ ሙዚቀኛው ራሱ መሆኑንም ለማረጋገጥ ንቅሳቶቹን ሲፈልጉ ነበር።
በሺዎች የሚቆጠሩ የሙዚቀኛው አድናቂዎችም ለስንብት ተገኝተው ነበር።
ቅዳሜ እለት ከመቀበሩ በፊት ለሙዚቀኛው አክብሮታቸውን ለመግለፅ በስታዲየም ኮንሰርት ተካሂዶ ነበር።
በቤተሰቡ ቤት ሽኝት የነበረ ሲሆን አስከሬኑን ለማየት የፈለጉ አድናቂዎችንም ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ ሲጠቀም ነበር ተብሏል።
"መቃብር ውስጥ ከመግባቱ በፊት የምንወደውን ሙዚቀኛ ማየት ፈልገን ነበር" በማለት አንድ አድናቂው ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጿል።
ፈረንሳይኛ በሚናገሩ ሃገራት ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው ዲጄ አረፋት የአይቮሪኮስት የዳንስ ሙዚቃ ተብሎ በሚጠራው ኩፔ ዴካልም ንጉስ የሚል ስያሜም ማትረፍ ችሏል።
በዘናጭነቱ የሚታወቀው ሙዚቀኛው ፈጣን የሆነ የከበሮ ምት፣ ሂፕሆፕ ቅላፄ ባለው ዘፈኖቹ ብዙ አድናቂዎችን ማትረፍ ችሏል።
ከመድረክ ውጭ ባለ ህይወቱ አወዛጋቢ የሆነው ሙዚቀኛው ቤት ውስጥ ጥቃትን በማድረስ ውንጀላዎች ቀርበውበታል።